ዩናይትድ ኪንግደም ፣ አሜሪካና አውስትራሊያ የቻይናን ተፅዕኖ ለመከላከል ተስማሙ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Defence
ዩናይትድ ኪንግደም ፣ አሜሪካ እና አውስትራሊያ የቻይናን ተፅዕኖ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የተራቀቁ የመከላከያ ቴክኖሎጂን ለመጋራት ልዩ የደህንነት ስምምነት አስተዋወቁ።
የሦስትዮሽ ስምምነቱ አውስትራሊያን ለመጀመሪያ ጊዜ በኑክሌር ኃይል የሚሰሩ ሰርጓጅ መርከቦች ለመስራት ያስችላታል።
'አውኩስ' የተባለው ስምምነት ሰው ሰራሽ ልህቀት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ)፣ የኳንተም ቴክኖሎጂንና ሳይበርን የሚያካትት ነው።
ሦስቱ አገራት የሕንድ ውቅያኖስንና የፓስፊክ ውቅያኖስን በሚያገናኘው [ኢንዶ -ፓስፊክ] አካባቢ የቻይና አቅም ማደግና ወታደራዊ ስምሪት መኖሩ አሳስቧቸዋል።
በስምምነቱ ምክንያትም አውስትራሊያ በፈረንሳይ ዲዛይን ሰርጓጅ መርከቦችን ለማሰራት የነበራትን ስምምነት ሰርዛለች።
ፈረንሳይ እአአ በ2016 ለአውስትራሊያ የባህር ኃይል 12 ሰርጓጅ መርከቦችን ለመስራት የ50 ቢሊየን የአውስትራሊያ ዶላር ውል አሸንፋ ነበር።
ስምምነቱ አውስትራሊያ በታሪኳ ያደረገችው ከፍተኛው የመከላከያ ስምምነት ነበር።
ሆኖም ፕሮጀክቱ አውስትራሊያ የመርከቦቹ አብዛኛው አካል በአገር ውስጥ እንዲመረቱ በመፈለጓ ምክንያት ከፍተኛ መዘግየት አጋጥሞታል።
ረቡዕ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን፣ የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እና የአውስትራሊያ አቻቸው ስኮት ሞሪሰን 'አውኩስ' የሚል ስያሜ የተሰጠውን የአዲሱን የደህንነት ስምምነት በተመለከተ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
" በአውኩስ ሥር እንደ መጀመሪያ ኢንሸቲቭስ እኛ ለሮያል አውስትራሊያ የባህር ኃይል የኑክሌር ኃይል ያላቸው ሰርጓጅ መርከቦችን እንድታገኝ አውስትራሊያን ለመደገፍ በጋራ እንሰራለን" ብለዋል በመግለጫቸው።
ይህ አቅም በኢንዶ-ፓስፊክ ያለውን መረጋጋት ለማሳደግ እንዲሁም የሚጋሯቸውን እሴቶችና ፍላጎቶች ለመደገፍ እንደሚውልም ገልጸዋል።
መሪዎቹ የስምምነቱ ዓላማ የአውስትራሊያን አቅም በተቻለ ፍጥነት ወደ አገልግሎት ማምጣት መሆኑን ጠቅሰው፤ አውስትራሊያ እንደ ኑክሌር ያልሆነ የጦር መሣሪያ ግዛትነቷ ሁሉንም ግዴታዎች ለመወጣት ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
አክለውም የመከላከያ ስምምነቱ በሳይበር ፣ በሰው ሰራሽ ልህቀት እና የባህር ውስጥ አቅም ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።












