ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አለማየሁ እሸቴ፡ ስለድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ ህልፈት ማን ምን አለ?
አንጋፋው ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ በልብ ህመም ምክንያት ትናንት ነሐሴ 27/2013 ዓ.ም በ79 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
የድምጻዊውን ህልፈት ተከትሎም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ የተሰማቸውን ሐዘን እየገለፁ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕመድ በድምጻዊው ሞት የተሰማቸውን ሐዘን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልፀዋል።
"ሀገሩን አጥብቆ በመውደድና ለሀገሩ ከልብ በመሥራት ለብዙ ከያንያን አርአያ የሆነው ዓለማየሁ እሸቴ ማረፉን ሰምቼ እጅግ አዝኛለሁ። ሰሞኑን ወጣትና አንጋፋ ከያንያን ስለ ኢትዮጵያ ዘመኑን የዋጀ ሙዚቃ እንዲያወጡ ሲያስተባብር እንደነበር አውቃለሁ። ሥራዎቹ ኢትዮጵያን ከፍ እንዳደረጉ ይኖራሉ። ለኢትዮጵያ የሠራ ያርፋል እንጂ አይሞትም" ሲሉ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለድምጻዊው ያላቸውን አክብሮትና ፍቅር የገለጹት።
የአዲስ አባባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤም በድምጻዊው ህልፈት የተሰማቸውን ገልፀዋል።
ምክትል ከንቲባዋ "አለማየሁ እሸቴ ለሚወዳት ኢትዮጵያ በጥበብ ሥራዎቹ ብዙ ያደረገ ሃገር ወዳድ ባለሙያ ነበር" ሲሉ ነው የገለፁት።
ወ/ሮ አዳነች ለድምጻዊው ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና አድናቂዎች መጽናናትን ተመኝተዋል።
ድምጻዊ ሚካኤል በላይነህ
ድምጻዊ ሚካኤል በላይነህ "የኢትዮጵያ ሙዚቃ አንዱን፣ ደማቁን ሰው፣ በቃ ተሰናበተ" ሲል ነበር ሃዘኑን የገለፀው።
ሚካኤል "ይህች ከንቱ ዓለም አንድ ውድ ሰው መሸኘቷን በሌሊቱ አሰማችን። አሌክስ እንግዲህ የተቆረጠችን ቀን ማን ያልፋታል? እኛስ ሰምቶ በተሰበረ ልብ ከመቀበል ውጭ ምንስ ኃይል አለን?" ሲልም ጠይቋል።
አለማየሁ በሙዚቃ ሕይወቱ ታላቅ ተግባር እንዳከናወነ የገለፀው ድምጻዊ ሚካኤል፤ "በተለየው ድምፅህ፣ ልዩ በሆነው መድረክ አያያዝህ፣ ፍፁም የራስህ ቀለም በሆኑት ዜማዎችህ አለማየሁ እሸቴ የተባለ ታላቅ ስም አኑረሀል። ስለዚህ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ በተለየ አሻራ ህያው ሆነህ ለትውልድ እንደምትተላለፍ ጥርጥር የለውም" ብሏል።
ሚካኤል ለድምጻዊ አለማየሁ ባለቤት፣ ልጆቹና ለመላው ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ መጽናናትን ተመኝቷል።
ፒያኒስት ሳሙኤል ይርጋ
በፒያኖ ተጨዋችነቱ የሚታወቀው ሳሙኤል ይርጋም በድምጻዊው ሞት የተሰማውን ሐዘን ከገለፁት መካከል ነው።
"ጋሽ አለማየሁ እሸቴ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ እጅግ በጣም ከልቤ አዝኛለሁ። ታላቅ ኢትዮጵያዊ የጥበብ ሰው ነበር። በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ መቼም የማይረሳ ሥራን ለሀገራችን ያበረከተ ታላቅ ሰው ነበር" ሲል እርሱንም እንደ አባት ያበረታው እንደነበር አውስቷል።
"አብረን በተጫወትንባቸው ጊዜያት ሁሉ እጅግ በጣም ደስተኛ ሆነን ብዙ አዳዲስ ሥራዎች ለመስራት ስናቅድም ነበር። መቼም ሞት ቀጠሮ የለውም እና ይህን ታላቅ ሰው በድንገት አጣነው። ነፍሱን በገነት ያኑርልን" ብሏል ፒያኒስት ሳሙኤል።
የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሃት
ሰርፀ ፍሬስብሃት ከሳምንት በፊት በ'ዐዲስ ወግ' የውይይት መድረክ ላይ በክብር አንግድነት ተጋብዞ ሁሌም ከሚታወቅበት ዘናጭነቱና ኩሩ አረማመዱ ጋር አግኝቶት እንደነበር በማስታወስ ነበር በድምጻዊው ህልፈት ማዘኑን በፌስቡክ ሰሌዳው የገለፀው።
"ወደ ውይይት መድረኩ ከገባን በኋላም ወደ መድረክ ተጋብዞ በሚገርም የሀገር ፍቅር የተመላ መልዕክቱን በርቱዕ አንደበቱ አቀረበ። ለካ ያ ንግግር የመጨረሻው ነበር" ብሏል ሰርፀ ሀዘኑን ባሰፈረበት ጽሁፉ።
ሰርፀ በዚሁ ጽሁፉ ድምጻዊ አለማየሁ በኢትዯጵያ ሙዚቃ የሬኮርዲንግ ታሪክ ውስጥ የተሳኩ እና ትራታቸው ከፍ ያሉ ከ400 በላይ ሥራዎችን ማበርከቱን ገልጿል።
አለማየሁ እሸቴ 'ጌሪ ኮፐር'፣ 'ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ'፣ 'አለማየሁ ቴክሱ፣ ነጭ ነው ፈረሱ' እየተባለም በአድማጮቹ የአድናቆት ቅፅሎች ይወደስ እንደነበርም አንስቷል።
አለማየሁ 'ወርቃማው' ተብሎ ለሚጠራው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘመን የመጀመሪያው ተጠቃሽ ድምጻዊ ነበርም ብሏል የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሃት።
በርካታ የጥበብ ባለሙያዎች፣ አድናቂዎችና ወዳጆች በድምጻዊው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን በማህበራዊ የትስስር ገጾች አሁንም እየገለፁ ይገኛሉ።