ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሮናልዶ፣ ኬን፣ ምባፔ፣ ግሪዝማን. . . የተሳኩትና ያልተሳኩት ዝውውሮች የትኞቹ ናቸው?
ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ያደረገውን ዝውውር ጨምሮ የፕሪሚየር ሊጉን ክለቦች ከአንድ ቢሊየን ፓውንድ በላይ በዝውውር መስኮቱ አውጥተዋል።
አጠቃላይ ወጪው ግን ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት ቀንሷል።
ትልቁ ስምምነት ኒኮላ ቭላሲክ ከሲኤስኬኤ ሞስኮ ወደ ዌስትሃም በ26.8 ሚሊዮን ፓውንድ ያደረገው ሆኗል።
በአጠቃላይ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች በዝውውር መስኮቱ 1.1 ቢሊዮን ፓውንድ ወጪ አድረገዋል። ከቀዳሚው ዓመት የ1.3 ቢሊዮን ፓውንድ ዝውውር በ11 በመቶ ዝቅ ብሏል።
እንደ ፋይናንስ ድርጅቱ ዴይሎት ዘገባ ከሆነ ይህ ከ2015 ጀምሮ በፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ዝቅተኛ ጠቅላላ ወጪ ሆኖ ተመዝግቧል።
የመጨረሻው ቀን የፕሪሚየር ሊጉ ዝውውሮች የትኞቹ ናቸው?
ቶተንሃም ለባርሴሎናው ተከላካይ ኤመርሰን ሮያል 25.8 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጣ ሲሆን የመስመር ተጫዋቹ ዳንኤል ጄምስ ከማንችስተር ዩናይትድ በ25 ሚሊዮን ፓውንድ ሊድስን ተቀላቅሏል።
ብራይተን የስፔኑን ተከላካይ ማርክ ኩኩሬላን ከጌታፌ በ15.4 ሚሊዮን ፓውንድ አስፈርሟል። ሴኔጋላዊው አጥቂ አብደላህ ሲማ ወደ ስቶክ በውሰት ከመዛወሩ በፊት ከሲላቪያ ፕራግ በተመሳሳይ ብራይተንን ተቀላቅሏል።
ከቭላሲክ በተጨማሪ ዌስትሃም የአማካዩን አሌክስ ክራልን ከስፓርታክ ሞስኮ በውሰት አምጥቷል። ሌስተር በበኩሉ ከአርቢ ሌፕዢንግ የክንፍ ተጫዋቹን አዴሞላ ሉክማንን በአንድ ዓመት የውሰት ውል አስፈርሟል።
በርንሌይ ዌልሳዊውን ኮነር ሮበርትስን ከስዋንሲ በማምጣት በጥቂት ቀናት ውስጥ ሁለተኛውን ተከላካይ አስፈርሟል። ክሪስታል ፓላስ በበኩሉ አጥቂውን አድሰን ኢዶዋርድን ከሴልቲክ በ15 ሚሊዮን ፓውንድ አዘዋውረዋል።
አርሴናል የጃፓኑን ተከላካይ ታሂሮ ቶሚያሱን ከቦሎኛ አስፈርሟል። በውሰት ደግሞ አርሰናል ሄክቶር ቤለሪን ወደ ሪያል ቤቲስና ሬይስ ኔልሰን ወደ ፌይኖርድ እንዲዛወሩ ፈቅደዋል።
ሰሎሞን ሮንዶን በነጻ ዝውውር ለኤቨርተን ፊርማውን አኑሯል።
ሜክሲኳዊው አጥቂ ሳንቲያጎ ሙኖዝ ደግሞ ወደ ኒውካስል አቅንቷል።
የአውሮፓ ዋና ዋና ዝውውሮችስ ምን ይመስላሉ?
ዋና ዋናዎቹ የአውሮፓ ክለቦች በዝውውሩ መጠናቀቂያ ዕለት ንቁ ተሳትፎ ቢኖራቸውም ሪያል ማድሪድ ምባፔን ለማስፈረም ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
የስፔኑ ግዙፍ ክለብ የፈረንሳዩን አማካይ ኤድዋርዶ ካማቪንጋን ከሬንስ አስፈርሟል።
ሮናልዶን በማንችስተር ዩናይትድ የተነጠቁት ጁቬንቱሶች አጥቂው ሞይስ ኬንን ከኤቨርተን በሁለት ዓመት የውሰት ውል እንደገና ማስፈረም ችለዋል።
ባርሴሎና ያሉበትን የፋይናንስ ስጋቶችን ለማቃለል ተጫዋቾችን የለቀቀ ሲሆን ኢላይክስ ሞሪባን ለአርቢ ሌፕዢንግ አሳልፎ ሲሰጥ አንቶኒ ግሪዝማን ደግሞ በውሰት ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ ተመልሷል።
ትልልቆቹ ዝውውሮች የትኞቹ ናቸው?
አርሰናል፣ ማንችስተር ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ቼልሲ አራቱ ከፍተኛ ገንዘብ ያወጡ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ሆነዋል።
ማንቸስተር ሲቲ ትልቁን የዝውውር መስኮቱን ስምምነት የእንግሊዝን የዝውውር ክብረ ወሰንን በመስበር ጃክ ግሪሊሽ ከአስቶን ቪላ በ 100 ሚሊዮን ፓውንድ የግሉ አድርጓል።
የአውሮፓ ሻምፒዮኑ ቼልሲ ደግሞ አጥቂውን ሮሜሎ ሉካኩን ከኢንተር ሚላን በ97.5 ሚሊዮን ፓውንድ መልሶ አስፈርሟል።
ማንችስተር ዩናይትድ ጄደን ሳንቾን ከዶርትመንድ በ 73 ሚሊዮን ፓውንድ እና ራፋኤል ቫራንን ከሪያል ማድሪድ በ34 ሚሊዮን ፓውንድ ኦልድ ትራፎርድ አድርሷል።
አርሰናል በዝውውር መስኮቱ ከፍተኛ ገንዘብ ካወጡ ክለቦች አንዱ ነበር። ቤን ዋይት ከብራይተን (50 ሚሊዮን ፓውንድ)፣ ማርቲን ኦዴጋርድ ከሪያል ማድሪድ (30 ሚሊዮን ፓውንድ) እና አሮን ራምስዴል ከሸፊልድ ዩናይትድ (24 ሚሊዮን ፓውንድ) ጨምሮ ሌሎችንም ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ቀላቅሏል።
ሊቨርፑል በአንጻራዊ ሁኔታ የተቀዛቀዘ የዝውውር መስኮት አሳልፏል። ተከላካዩን ኢብራሂማ ኮናቴን ከአርቢ ሌፕዢንግ ለማስፈረም 36 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥቷል።
በመጨረሻው የዝውውር ቀን የአራት ዓመት ውል የፈረመውን አምበሉን ጆርዳን ሄንደርሰን ጨምሮ ለበርካታ ቁልፍ ተጫዋቾቹን ውል አራዝሟል።
በጣም ትኩረት የሳበው ዝውውር ሊዮኔል ሜሲ ለ21 ዓመታት ከቆየበት ባርሴሎና በነጻ ዝውውር ወደ ፓሪስ ሴንት ዠርሜን ያቀናበት ሆኗል።
ያልተሳኩት ዝውውሮችስ?
የ2021 የክረምት የዝውውር መስኮት ባልተሳኩ ስምምነቶችም ይታወሳል።
ማንችስተር ሲቲ አብዛኛውን የዝውውር መስኮት የእንግሊዙን አምበል ሃሪ ኬንን ለማዘዋወር ጥረት ቢያደርግም አጥቂው በስፐርስ ለመቆየት ተስማምቷል።
ሪያል ማድሪድ ምባፔን ለማስፈረም ሁለት ጊዜ ሞክሯል። ማድሪዶች ሁለት ጊዜ ከ100 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ያቀረቡት ዋጋ በፓሪስ ሴንት ዠርሜን ውድቅ ተደርጓል።
ቼልሲ ፈረንሳዊውን ተከላካይ ጁልስ ኩንዴን ለማስፈረም ቢፈልግም ሲቪያ ከመሸጫ ዋጋው 80 ሚሊዮን ዩሮ በታች ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
አይንስሊ ማይትላንድ-ኒልስ ማህበራዊ ድር አምባውን ተጠቅሞ ከአርሰናል ለመልቀቅ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
የጄሴ ሊንጋርድ ወደ ዌስትሃም የታቀደው ዝውውር ባለመሳካቱ በማንችስተር ዩናይትድ ይቆያል። ዎልቭስም የሊሉን አማካይ ሬናቶ ሳንቼዝን ዘግይቶ ለማዘዋወር ያደረገውን ጥረት አቋርጧል።