ካናዳዊው ነጋዴ ቻይና ውስጥ ሰልለሃል ተብሎ በ11 ዓመት እሥር ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አንድ የቻይና ፍርድ ቤት ካናዳዊውን ነጋዴ መረጃ አሳልፎ በመስጠት ወንጀል ጥፋተኛ ነው ብሎ በ11 ዓመት እሥር ቀጥቶታል።
ማይክል ስፓቮር በፈረንጆቹ 2018 ነው ከካናዳዊው የቀድሞ ዲፕሎማት ጋር በቁጥጥር ሥር የዋለው።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ግንኙነታቸው እየሻከረ ለመጣው ካናዳና ቻይና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል እየተባለ ነው።
የቻይናው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሁዋዌ ነባር ሥር አስፈፃሚ የሆኑት ቻይናዊው ሜንግ ዋንዡ የፍርድ ሂደት እየታየ ያለው ካናዳ ውስጥ እንደሆነ ይታወቃል።
ተቺዎች ቻይና ስፓቮርንና ኮቭሪግን ይዛ ለፖለቲካ ጥቅሟ አውላቸዋለች ሲሉ ይወቅሳሉ።
ዕለተ ረቡዕ መግለጫ ያወጣው የዳንዶንግ ፍርድ ቤት "ስፓቮር ለፈፀመው የስለላና የአገር ምስጢር አሳልፎ የመስጠት ወንጀል በ11 ዓመት እሥር እንዲሁም በ50 ሺህ የቻይና ዩዋን እንዲቀጣ አልፎም ከአገር እንዲባረር ተወስኗል" ይላል።
መግለጫው ግለሰቡ መቼ ከቻይና እንደሚባረር በግላጭ ያለው ነገር ባይኖርም፤ ቻይና የተፈረደባቸው የውጭ አገራት ዜጎችን ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ ነው ከአገር የምታስወጣው።
በቻይና የካናዳው አምባሳደር ዶሚኒክ ባርተን ውሳኔውን እንደሚቃወሙት አስታውቀዋል። "ይግባኝ ለመጠየቅ ዕድል ይኖራል" ማለታቸውን ኤኤፍፒ የተሰኘው የዜና ወኪል ዘግቧል።
ስፓቮር ከ3 ዓመት በፊት በቁጥጥር ሥር የዋለው ልክ ሜንግ የተሰኘው የሁዋዌ ሥራ አስፈፃሚ ሲያዝ ነበር።
ሰውዬው ባለፈው መጋቢት ፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሳይሰጥበት ችሎቱ ተበትኗል። በወቅቱ የካናዳ ዲፕሎማቶች ወደ ችሎቱ መግባት እንዳይቸሉ ታግደው ነበር።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ችሎቱ በዝግ መካሄዱን "በፍፁም ተቀባይነት የሌለው" ብለውት ነበር።
ቻይና ከስፖቮርና ከሌላኛቸው ካናዳዊ ዲፕሎማት በተጨማሪ ሌሎች ካናዳዊያንንም በተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥሪያለሁ ብላ በቁጥጥር ሥር አውላ ነበር።
የፖለቲካ ተንታኞች ቻይና ይህን ያደረገችው ካናዳ የሁዋዌውን ሥራ አስፈፃሚ እንድትለቅ ለማስገደድ ነው ይላሉ።












