የሜክሲኮ አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎች የቴሌቪዥን ዜና አቅራቢዋን እንደሚገድሉ ዛቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በሜክሲኮ እጅግ ከሚፈሩት አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎች አንዱ የሆነውና በምሕጻሩ ሲጄኤንጄ የሚባለው የቦዘኔዎች ቡድን የቴሌቪዥን ዜና አንባቢዋን እንደሚገድል ዛተ፡፡
የጃሊስኮ ኒው ጄኔሬሽን የአደገኛ እጽ ሰንሰለት (ሲጄኤንጄ) ቃል አቀባይ ነኝ ያለ ግለሰብ ፊቱን በጭምብል ሸፍኖ ለዓለም ባሰራጨው የዛቻ ቪዲዮ እንዳለው ጋዜጠኛዋ እንድትገደል የተወሰነው በዘገባዎቿ ሚዛናዊ አይደለችም በሚል ነው፡፡
የሚሌኒዮ ቴሌቪዥን ዜና አንባቢ የሆነችው ሚስ አሴና ኡረስቲ ይህን አደገኛ እጽ ሰንሰለት የቦዘኔዎች ቡድንን ለመመከት የተቋቋሙትን ራስን የመከላከል ቡድንን በዘገባዎቿ ትደግፋቸዋለች ሲል ክስ ያቀረቡባት፡፡
ጋዜጠኛዋ በቀጥታ እንደምትገደል በቪዲዮ የተዛተባት ሲሆን ‹የተናገርሻቸውን ቃላት ቅርጥፍጥፍ አድርገሽ መልሰሽ እንደትጎርሻቸው እናደርጋለን› ብሏታል፣ የአደገኛ ቦዘኔዎቹ ቡድን ቃል አቀባይ፡፡
የአደገኛ ቦዘኔዎቹ ቃል አቀባዩ የሚዲያና የመናገር ነጻነትን እንደሚያከብሩ ያስገነዘበ ሲሆን ነገር ግን ለኛ የሚሰጠን የዜና ሽፋን የተንሻፈፈና ከሚዛናዊነት የራቀ ነው ሲል ቅሬታውን አቅርቧል፡፡
ለዚህ አጸፋ ደግሞ ጋዜጠኛዋን እንገድላለን ብሏል፡፡
በሜክሲኮ አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎችን ለመመከት ራስን የመከላከል ቡድኖች በየሰፈሩ ይደራጃሉ፡፡
በዚህ መንገድ ራሱን አደራጅቶ አደገኛ ቦዘኔዎቹን በመከላከል የተመሰረተ ቡድን ስኬታማ ስራ መስራቱን ይነገራል፡፡
እጽ አዘዋዋሪዎቹ እንደሚሉት ግን ይህ ቡድን ራሱ ሌላ ተገዳዳሪ የአደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎች የፈጠሩት አደገኛ ቡድን ነው፡፡
በጋዜጠኛዋ ዛቻ የሰነዘረው ሲጄኤንጄ የአደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎች ሰንሰለት የሚመራው በሞገደኛው ነሜሲዮ ኦሴጉዋሬ ሰርቫንቴስ ሲሆን በሜክሲኮ ቁጥር አንድ በወንጀል ተፈላጊ ሰው ነው፡፡
አሜሪካም ግለሰቡ ያለበትን ለጠቆመኝ 10 ሚሊዮን ዶላር እሸልመዋለሁ ብላለች፡፡
ሜክሲኮ ጋዜጠኛ መሆን እጅግ አደገኛ ከሆነባቸው አገሮች አንዷ ናት፡፡
በየስርቻው ጋዜጠኞችን ገድሎ መጣል በሜክሲኮ የተለመደ ቢሆንም እንዲህ በአደባባይ መግለጫ መስጠት ግን እምብዛምም የተለመደ አልነበረም፡፡












