ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስትወለድ በክብደት የዓለማችን ትንሿ ጨቅላ የነበረችው ከዓመት በኋላ ከሆስፒታል ወጣች
ስትወለድ ከአንድ ብርቱካን ያነሰ ክብደት ትመዝን የነበረችው የዓለማችን ጨቅላ ከ13 ወራት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ ወደ ቤቷ ገባች።
እምቦቅቅላዋ በሲንጋፖር ሆስፒታል ባለፉት 13 ወራት በጽኑ ሕሙማን ክፍል ክትትል ሲደረግላት ቆይቷል።
ዌክ ዩ ዥዋን ትባላለች። ስትወለድ የምትመዝነው 212 ግራም ነበር። ይህ ክብደት ማለት በአማካይ የአንድ ትንሽ ብርቱካን ክብደት ማለት ነው። ቁመቷ 24 ደግሞ ሴትቲ ሜትር ብቻ ነበር።
አንድ ጤናማ ልጅ የሚወለደው በአማካይ ከ40 ሳምንታት ቆይታ በኋላ መሆኑ ይታወቃል። ይህቺ ልጅ የተወለደችው ግን ያለ ጊዜው በ25 ሳምንቷ ነበር።
እስከዛሬ ስትወለድ የዓለማችን በኪሎ ትንሿ ትባል የነበረችው ልጅ አሜሪካዊት ነበረች። ይህች ልጅ ስትወለድ 245 ግራም ነበር የምትመዝነው።
ይህ ክብረ ወሰን አሁን በሲንጋፖሯ ጨቅላ ተሻሽሏል።
የዚህች ደቃቃ ልጅ እናት ልጇን የተገላገለቻት በቀዶ ህክምና ነበር። ለመውለድም ገና አራት ወራት ሲቀራት ነበር የተገላገለቻት።
ከ13 ወራት ከፍተኛ ክትትል በኋላ አሁን የጨቅላዋ ክብደት 6.3 ኪሎ ግራም ሆኗል።
የሲንጋፖር ብሔራዊ ሆስፒታል ይህቺ ልጅ በተወለደች ወቅት በሕይወት የመኖር ዕድሏ በጣም ጠባብ ነበር ይላል።
በሆስፒታል ቆይታዋ በሕይወት እንድትቆይ የተለያዩ ሕክምናዎች እና የሕክምና ድጋፎች አስፈልገዋት ነበር። ዶክተሮች ጨቅላዋ እድገቷ አጥጋቢ በመሆኑ ከሆስፒታል እንድትወጣ መወሰኑን ተናግረዋል።
ጨቅላዋ ዌክ ዩ ዥዋን አሁንም ቢሆን የከፋ የሳምባ ሕመም ያለባት ሲሆን ወደቤት ከተሰወደችም በኋላ ለመተንፈስ ድጋፍ ያስፍልጋታል ተብሏል። ሐኪሞች ጨቅላዋ ከሳምባ ሕመሟ እንደምታገግም ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።
የልጅቷ እናት ከዚህ ቀደም የወለዱት ልጅ ጤናማና መደበኛ ኪሎ የሚያሟላ ነበር።
የዚህች ደቃቃ አራስ ልጅ የሆስፒታል ወጪ ከፍተኛ ሲሆን ገንዘቡን የሸፈኑት ግን ከሕዝብ በተሰበሰበ ዘመቻ ነው።
ለዚህች በኪሎ ዝቅተኛ ለተባለችው የዓለማችን እንቦቀቅላ በአጭር ጊዜ 270ሺህ ዶላር ተሰብስቦላታል።