ቻይና በአሜሪካ ባለሥልጣናትና ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጣለች

ቻይና ማዕቀብ ከጣለችባቸው የአሜሪካ አመራሮች መካከል የቀድሞው የንግድ ዘርፍ ጸሐፊ ዊልበር ሮስ ይጠቀሳሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ቻይና በበርካታ የአሜሪካ ባለሥልጣናትና ተቋማት ላይ ማዕቀብ እየጣለች ትገኛለች። ይህም አሜሪካ በሆንግ ኮንግ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ለመጣሏ የመልስ ምት ነው።

ቻይና ማዕቀብ ከጣለችባቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት መካከል የቀድሞው የንግድ ዘርፍ ጸሐፊ ዊልበር ሮስ ይጠቀሳሉ። ቻይና ማዕቀብ መጣል የጀመረችው የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዌንዲ ሸርማን ቻይናን ለመጎብኘት ቀናት ሲቀናቸው ነው።

አሜሪካ በሆንግ ኮንግ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ የጣለችው በዜጎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች በሚወስዱት እርምጃ እጃቸው አለበት በሚል ነው። ሆንግ ኮንግ ውስጥ የሚነግዱ አሜሪካውያን በግዛቲቱ የደኅንነት ስጋት እንዳለም ተነግሯቸዋል።

ቻይና በሆንግ ኮንግ ብሔራዊ የደኅንነት ሕግ ያወጣችው ባለፈው ዓመት ነበር። በሆንግ ኮንግ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች ሲበራከቱ ነበር ሕጉ የወጣው።

ሕጉ ከውጭ አገራት ጋር መመሳጠርን፣ ግዛቲቱ የመገንጠል ጥያቄ ማንሳትን በወንጀልነት ፈርጆ ይቀጣል።

በእነዚህ ወንጀሎች የተከሰሱ ዜጎች እስከ እድሜ ልክ እስራት ድረስ ሊቀጡ ይችላሉ።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳለው፤ አሜሪካ በሆንግ ኮንግ ባለሥልጣናት ላይ የጣለችው ማዕቀብ "የሆንግ ኮንግን ንግድ ለማቀዛቀዝ ያለመ" ነው።

ማዕቀቡ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጣረስ እንዲሁም የአገራትን የግንኙነት መርህ የጣሰ መሆኑንም ቻይና ተናግራለች።

በቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥር የንግድ ዘርፍ ጸሐፊ የነበሩት ዊልበር ሮስ፤ ሁዋዊ እና ዜድቲኢን ጨምሮ ሌሎችም የቻይና ድርጅቶች ከአሜሪካ ጋር ያለ ፍቃድ እንዳይነግዱ የሚያግድ መመሪያ አውጥተዋል።

ከዊልበር ሮስ በተጨማሪ ቻይና ማዕቀብ የጣለችው የመብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች የቻይና ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ሶፊ ሪቻርድሰን ላይ ነው።

የቻይና እና አሜሪካ የምጣኔ ሀብትና ደኅንነት ኮሚሽን ኃላፊ ካሮሊን ባርቶሎሜው፣ የዓለም አቀፉ የሪፐብሊካን ተቋም አመራር አዳም ኪንግ ላይም ማዕቀብ ተጥሏል።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ አሜሪካ በቻይና ማዕቀብ "አትበገርም" ብለዋል።

"እነዚህ ማዕቀቦች ቻይና ዜጎች፣ ተቋሞችና የሲቪል ማኅበራትን በመቅጣት የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር እንደምትሞክር ማሳያ ናቸው" ሲሉም ቃል አቀባይዋ ምላሽ ሰጥተዋል።

በትራምፕ የአስተዳደር ዘመን የአሜሪካ እና የቻይና ግንኙነት ከመቼውም በባሰ መሻከሩ አይዘነጋም።

የኮሮናቫይረስ መነሻ፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲሁም የበይነ መረብ ደኅንት ጥበቃ ቻይና እና አሜሪካን ከሚያወዛግቡ ጉዳዮች ጥቂቱ ናቸው።

ከሰሞኑ የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዌንዲ ሸርማን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማለሳለስ ወደ ቻይና ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጆ ባይደን ፕሬዘዳንት ከሆኑ በኋላ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ወደ ቻይና ሲያቀና ይህ የመጀመሪያው ነው።

ቻይና የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚንስተር ማይክ ፖምቶዮን ጨምሮ 27 የትራምፕ ዘመን አመራሮች ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።

የባይደን አስተዳደር ይህንን እርምጃ "ፍሬ አልባና ጨለምተኛ" ብሎታል።