ሚሊዮኖችን ለሞት የዳረጉ ወረርሽኞችና የመከላከያ ክትባቶቻቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኮሮናቫይረስ፤ ወረርሽኞች ምን ያህል ገዳይ እንደሆኑ አሳይቶናል። ያለው አማራጭ ደግሞ ክትባትና ክትባት መሆኑን አሁን ልናይ ነው።
ኮሮናቫይረስ ለክትባት እጁን የሰጠ የመጀመሪያው በሽታ አይደለም።
በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድ ወቅት ልክ እንደ ኮሮናቫይረስ ካሉ ገዳይ በሽታዎች ማምለጥ ችለዋል።
ነገር ግን ማኅበረሰብን ከሚያሸብሩ በሽታዎች በዕድልም ቢሆን ለማምለጥ የሚኖሩበት አድራሻ ወሳኝ ነው። ክትባቱን ሳያገኙ ብዙዎች አልፈዋልና።
ፈንጣጣ
ፈንጣጣ ክትባት አይበግረኝም ብለው ካስቸገሩ ወረርሽኞች አንዱ ነው። በስተመጨረሻ ግን ጨርሶ የሚምር ክትባት ተገኝቶለታል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ብቻ ፈንጣጣ ከ300 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ገድሏል። ከዚያ በፊት ባለው ጊዜ ደግሞ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታው እንደሞቱ ይገመታል።
በፍጥነት በሚዛመተው የፈንጣጣ ወረርሽኝ ከተያዙ ሰዎች መካከል 30 በመቶው እንደሞቱ ይነገራል።
ከበሽታው የተረፉ ደግሞ ዓይናቸው ሊታወር ይችላል፤ አሊያም ሰውነታቸው ላይ የማይሽር ጠባሳ ይኖራል።
ይህንን ገዳይ ወረርሽኝ ለመግታት ለዓመታት በርካታ ሙከራ ተደርጓል። ለበሽታው መድኃኒት የተገኘለት ከብዙ ክፍለ ዘመናት በኋላ ነው።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1000 ዓመት ቻይና ውስጥ አንድ ባሕላዊ መድኃኒት ተሞክሮ እንደነበር ይነገራል። ሳዑዲ አራቢያና አፍሪካ ውስጥ ለበሽታው መድኃኒት ለማግኘት የጊዜው አዋቂዎች ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።
የእንግሊዝና ቱርክ የጤና ባለሙያዎችንም ለፈንጣጣ ክትባት ለማግኘት ብዙ ወጥተው ወርደዋል።
እንግሊዛዊው ኤድዋርድ ጄነር ሰዎችን ከበሽታው ለማዳን ራሱ በሽታው ጠቃሚ መሆኑን የተረዳ የመጀመሪያው ሰው ነው።
ለበሽታው ክትባት እንደተገኘለት አገራት 80 በመቶ ሕዝባቸውን እንዲያስከትቡ ታቅዶ ነበር። ነገር ግን ይህ በቀላሉ የሚሳካ አልሆነም።
ይህ ሳይሳካ ሲቀር በሽታው ታይቶበታል የተባለበት አካባቢ በመሄድ በሥፍራው ያሉ ሰዎችን መከተብ አዋጭ ሆኖ ተገኘ።
በናይጄሪያ ብቻ 12 ሚሊየን ሰዎችን ከፈንጣጣ መታደግ የተቻለው 750 ሺህ ሰዎች እንዲከተቡ በማድረግ ነው።
አሁን የፈንጣጣ በሽታ ዓለም ላይ ሁለት ቦታዎች ብቻ ነው ያለው። አንደኛው ሩስያ ውስጥ ያለ በደንቡ የሚጠበቅ ቤተ-ሙከራ ውስጥ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አሜሪካ ባለ ተመሳሳይ ቤተ ሙከራ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፖሊዮ [የልጅነት ልምሻ]
ከፈንጣጣ ጋር ሲነፃፀር ፖሊዮ ሕይወት ያሳጣቸው የዓለማችን ሰዎች ቁጥር አናሳ ነው።
በብዛት ሕፃናትን የሚያጠቃው የፖሊዮ ወረርሽኝ በአፍ በሚተላለፍ ቫይረስ የሚዛመት ነው። ወደ ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ የነርቭ ሥርዓትን ያጠቃል፤ ፖሊዮ።
የፖሊዮ ወረርሽኝ ከ200 ተጠቂ አንድ ሰው ላይ ልምሻ ያስከትላል። በአብዛኛው ጊዜ ደግሞ እግር አካባቢን ያጠቃል።
ልምሻ ከያዛቸው 10 ሰዎች መካከል ቢያንስ አንድ ሰው በመተንፈሻ ጡንቻ ሕመም ምክንያት ይሞታል።
ፖሊዮ ልዩ የሆኑ የሕመም ምልክቶች እምብዛም ስለማያሳይ መድኃኒት ማግኘት ቀላል አልነበረም።
ነገር ግን በ1905 ስዊዲናዊው ዶክተር ኢቫር ዊክማን ፖሊዮ ተላላፊ በሽታ መሆኑን ማረጋገጥ ቻለ።
ይህ ግኝት የመጣው በበርካታ አገራት ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚጠጡት ውሃ ጥራት መሻሻል ሲጀምር ነው። በዚህ ምክንያት በፖሊዮ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያነሳ መጣ።
ያላደጉ በሚባሉ አገራት የፖሊዮ ወረርሽኝ ቁጥር ትንሽ ነው እየተባለ ቢነገርም ኋላ ላይ የተሠሩ ጥናቶች ግን ውጤታቸው የግምቱ ተቃራኒ ሆኖ ተገኘ።
ለፖሊዮ መድኃኒት የተገኘለት በ1952 ነበር። አሜሪካዊው ዶክተር ጆናስ ሳልክ የመጀመሪያውን ክትባት በመፍጠር ይታወቃል። ከዚያ በመቀጠል አልበርት ሳቢን በመርፌ ከሚሰጥ ይልቅ በአፍ የሚሰጥ ይሻላል በማለት የተሻሻለ ክትባት አስተዋወቀ።
ክትባቱ ብዙ ደረጃዎችን አልፎ አሁን በርካታ የዓለማችን አገራት ከፖሊዮ ነፃ ሆነዋል። 18 ሚሊዮን ሕፃናት በመከተባቸው ቆመው መራመድ ችለዋል። 1.5 ሚሊዮን ሞቶችን መታደግም ተችሏል።
ዛሬ ፖሊዮን በአፍጋኒስታን እና በፓኪስታን ውስጥ አልፎ አልፎ ከሚሰሙ ወረርሽኖች ባለፈ ከተቀረው ዓለም ጠፍቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኩፍኝ
የኢቦላ ቫይረስ በቅርብ ዓመታት ወረርሽኝ ሆኖ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ሲከሰት 20 ሺህ ገደማ ሰዎችን መግደሉ ይነገራል።
ነገር ግን ኩፍኝ በየዓመቱ 140 ሺህ ሰዎችን እንደሚገድል መረጃዎች ያሳያሉ።
ኩፍኝ ክትባት የተገኘለት በ1963 ነው።
በሳል፣ በማስነጠስ እና በንክኪ የሚተላለፈው ኩፍኝ ከባድ ትኩሳትና የቆዳ መቆጣት ያስከትላል።
ገዳዩ የኩፍኝ ወረርሽኝ ክትባት ሳይገኝለት በፊት በየዓመቱ 2.6 ሚሊዮን ሰዎችን ይቀጥፍ ነበር። አሁንም ቢሆንም ወረርሽኙ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተስፋፋ ይገኛል።
በአሜሪካና በአውሮፓ ብቻ በቅርብ ዓመታት በርካታ ሰዎች በኩፍኝ ወረርሽኝ እንደሞቱ ተነግሯል።
ነገር ግን የሚከተቡ ሰዎች ቁጥር አሁንም አናሳ ነው። ይህ የሆነው ሰዎች ክትባት የሚያመጣውን የጎንዮሽ ጉዳት በመሸሽ ለመከተብ ስለማይፈለጉ እንደሆነ ይነገራል።
ከ2019 ጀምሮ ባለው ጊዜ ብቻ ኩፍኝ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ውስጥ 7 ሺህ ሕፃናትን ፈጅቷል። እንደ ኮንጎ ባሉ አገራት ክትባቱን በነፃ ማግኘት ከባድ ነው።
ለዚህም ነው የዓለም ጤና ድርጅት 255 ሚሊዮን መድቡልኝና በሽታውን ላጥፋው ሲል ለአባል አገራቱ መልዕክት ያስተላለፈው።
ምንም እንኳ ኩፍኝን የሚከላከል ክትባት ቢገኝለትም ክትባቱን በማድረስ ረገድ የዓለም አገራት ተዘናግተዋል ተብለው ይተቻሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ወባ
በምንኖርባት ቢያንስ ግማሹ የዓለም ሕዝብ ለወባ በሽታ የተጋለጠ ነው። በየዓመቱ ቢያንስ 4 መቶ ሺህ ሰዎች በትንኝ አማካይነት በሚተላለፈው የወባ በሽታ ሕይወታቸውን ያጣሉ።
በወባ በሽታ ከሚከሰቱ ሞቶች 95 በመቶው የሚመዘገቡት አህጉረ አፍሪካ ውስጥ ነው።
ለወባ በሽታ የተዘየዱ የተለያዩ መላዎች አሉ። አንደኛው በመኝታ ዙሪያ አጎበር መዘርጋት ነው። በበሽታው ከተያዙ በኋላም የሚዋጡ መድኃኒቶች አሉ።
ነገር ግን ጥገኛ ሕዋሱም ሆነ ትንኞች የበሽታ መከላከያዎችን እየተላመዱት ይመጣሉ።
ለወባ በሽታ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ክትባት አልተገኘለትም ነበር። ነገር ግን ከ32 ዓመታት ጥናት እና ከ700 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ፈሰስ በኋላ አንድ ክትባት ተገኝቶ ወደ ዕደላ እየተገባ ነው።
ክትባቱ በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በሽታው 40 በመቶ እንደሚከላከል ሙከራዎች አረጋግጠዋል። ቢሆንም ይህ የውጤታማነት አሃዝ ከሌሎች ክትባቶች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ዝቅ ያለ ነው።
ክትባቱ አራት ጊዜ ነው የሚሰጠው።
ቢሆንም የዘርፉ ሙያተኞች ክትባቱ እስኪሻሻል ድረስ የመጀመሪያው ዙር ውጤት መልካም ነው ይላሉ። በማላዊ፣ ጋና እና ኬንያ የሚኖሩ ሰዎችም ክትባቱ እየተሞከረባቸው ነው።
ሙከራው ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ይዘልቃል።














