ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሥመ ጥሩ ግብጻዊ ጋዜጠኛ በሕዳሴው ግድብ ዙርያ ፕሬዝዳንት አል ሲሲን በመተቸቱ ዘብጥያ ወረደ
በግብጽ ገናና ስም ካላቸው ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው አብዱናስር ሰላማ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲን ከሥልጣን ይልቀቁ ሲል በይፋ በመናገሩ ዘብጥያ ወረደ፡፡
የግብጽ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ጋዜጠኛው አሁን የሽብር ክስ ተከፍቶበታል፡፡
ጋዜጠኛ ሳላማ የቀድሞው ዕለታዊው አል አሕራም ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር፡፡
ከሰሞኑ በግል ፌስቡክ ገጹ ላይ አልሲሲ ከኢትዮጵያ በተለይም ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያሳዩት ቸልተኝነት አስቆጥቶት ትችት ከጻፈ በኋላ ነው ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን እንዲለቁ የገለጸው፡፡
ግብጽ ኢትዮጵያ የምትገነባውን ግዙፉን የሕዳሴ ግድብ የውሃ ድርሻዬን ክፉኛ ይጎዳዋል በሚል በስጋት ነው የምትመለከተው፡፡ ሆኖም ግን ስጋቷን ለማስቀረት ከኢትዮጵያ ጋር አንዳች ስምምነት ላይ ለመድረስ ሳይቻላት ቀርቷል፡፡
ጋዜጠኛ ሰላማም ይህንኑ በማንሳት ነው አል ሲሲን በሰላ ትችት ከፍ ዝቅ አድርጓቸዋል የተባለው፡፡
ጋዜጠኛ ሰላማ ከትናንት በስቲያ እሑድ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ሽብርን በገንዘብ በመደገፍና ሕገወጥ ድርጅቶች ውስጥ አባል በመሆን ክስ ተመስርቶበታል፡፡
የመብት ተሟጋቾች የአልሲሲ መንግሥት ፕሬዝዳንቱን በሚተቹ ጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሰውን ማስፈራሪያና እንግልት እንዲያቆም በተደጋጋሚ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡