ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቻይና ሆቴል ተደርምሶ 17 ሰዎች ሞቱ
በምስራቅ ቻይና በምትገኘው ሱዙህ ከተማ አንድ የሆቴል ሕንጻ ተደርምሶ ቢያንስ 17 ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሕንጻው ከተደረመሰ በኋላ ለ36 ሰዓታት ባካሄዱት ፍለጋ የ17 ሰዎችን አስክሬን ሲያወጡ 6 ሰዎችን ደግሞ በሕይወት ከፍርስራሽ ስር አግኝተዋል።
ግሎባል ታይምስ እንደዘገበው ከሆነ ሕንጻው ሊደረመስ የቻለው የሕንጻው ባለቤት የሕንጻውን አወቃቀር ለመቀየር ጥረት በማድረጉ ነው።
የተደረመሰው ሕንጻ በቅርብ ዓመታት ብዙ እድሳቶች ተደርገውለት ነበር ተብሏል።
"ሕንጻው ሦስት ወለሎች ብቻ ነበሩት። በየጊዜው ግን ተጨማሪ ወለሎች ሲጨምሩበት ነበር" በማለት አንድ የአከባቢው ነዋሪ ሬድ ስታር ኒውስ ለተባለ መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።
የግዛቲቷ ባለስልጣናት በበኩላቸው የሕንጻውን መደርመስ በተመለከተ ምርመራ መጀመሩን ገልጸው ለሕንጻው መደርመስ ጥፋተኛ የሆኑ በወንጀል ይጠየቃሉ ብለዋል።
የሆቴሉ ሕንጻ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ሰኞ ከሰዓት ላይ የተደረመሰ ሲሆን ከፍርስራሹ ሥር ሰዎችን ለመታደግ ከ600 በላይ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሰማርተው ነበር።
54 መኝታ ክፍሎች ባሉት ሆቴል ውስጥ 23 እንግዶች ነበሩ የተባለ ሲሆን ከፍርስራሹ ስር ከወጡት 6 ሰዎች መካከል አንዱ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰበትም ተብሏል።
ብዙ ጊዜ በቻይና ለሚከሰቱ የሕንጻ መደርመሶች የሚሰጠው ምክንያት ጥራቱን ያልጠበቀ የግንባታ ሥራ ነው።
ከአንድ ዓመት በፊት ፉጂያን ተብላ በምትጠራ ግዛት በተመሳሳይ አንድ የሆቴል ሕንጻ ተደርምሶ 29 ሰዎችን ሕይወታቸውን አጥተዋል። መርማሪዎች ለሕንጻው መደርመስ ምክንያቱ ጥራቱን ያልጠበቀ የግንባታ ሥራ ነው ብለው ነበር።