ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማኅበራዊ ሚዲያ፡ ኡጋንዳውያን ለሚጠቀሙት የኢንተርኔት አገልግሎት ታክስ መክፈል ጀመሩ
ኡጋንዳውያን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ከዛሬ ሐሙስ ዕለት ጀምሮ የሞባይል ዳታ 12 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ መክፈል ጀመሩ።
ይህ ታክስ እአአ በ2018 የተዋወቀውና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጣለውን የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ዕለታዊ ታክስ [ኦቲቲ] ን ተክቷል።
አዲስ የተጣለው ኤክሳይዝ ታክስ ተግባራዊ መሆን የጀመረው አዲስ የበጀት ዓመት መጀመሩን ተከትሎ ነው።
ኤክሳይዝ ታክስ በተመረጡ እቃዎች ወይም አገልግሎቶች፤ በተለይም የቅንጦት ተብለው በሚታሰቡት ላይ የሚጣል ቀጥተኛ ያልሆነ የታክስ ዓይነት ነው።
ይህ ታክስ የተዋወቀው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በአገሪቱ ምክር ቤት ማሻሻያ ከተደረገበት በኋላ ነው።
ለሕክምና እና ለትምህርት አገልግሎት ለሚገዛ የሞባይል ዳታ ላይ ታክሱ አይጣልም ተብሏል። ይሁን እንጅ ይህንን አገልግሎት ከሌላው እንዴት መለየት እንደሚቻል ግልፅ ያለ ነገር የለም።
እአአ ሐምሌ 2018 የማኅበራዊ ሚዲያ ታክስ ተቃውሞን ቀስቅሶ ነበር።
ተቃውሞው በተቃዋሚው ፖለቲከኛውና ሙዚቀኛ ሮበርት ክያጉላኒ ወይም ቦቢ ዋይን የተመራ ነበር። በወቅቱ ተቃውሞው የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ተበትኗል።
አብዛኞቹ ኡጋንዳውያን ቪፒኤን የተባለውንና እገዳውን ለማለፍ የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን ኢንተርኔትን ለመጠቀም አማራጭ አድርገዋል።
በዚህም ምክንያት የሚጠበቀውን ያህል ግብር መሰብሰብ ሳይቻል ቀርቷል።
የአገሪቷ የገቢዎች ባለሥልጣን በ2018 - 2019 የበጀት ዓመት ለመሰብሰብ አቅዶ ከነበረው 80 ሚሊየን ዶላር፤ መሰብሰብ የቻለው 14 ሚሊየን ዶላር መሆኑን በዚያው ዓመት አስታውቆ ነበር።
ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ላይ ታክስ መጣል በኡጋንዳ፤ በተለይም አነስተኛ ንግዶችን ለመጀመር በብዛት ኢንተርኔትን የሚጠቀሙ ወጣቶችን አስቆጥቷል።