ኮሮናቫይረስ፡ ድመትና ውሾች ኮቪድ እንደሚይዛቸው ተደረሰበት

ታትሟል

የኮቪድ ቫይረስ በለማዳ የቤት ውስጥ እንሰሳት በተለይም በውሾችና በድመቶች ላይ በስፋት እንደሚገኝ አንድ ጥናት አመለከተ።

ጥናቱ እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው 196 የኮቪድ ተህዋሲ የጎበኘው ቤተሰብ ላይ ባደረገው ምርምር ነው።

በ196 አባወራዎች ላይ በተደረገው ይህ ምርምር 310 ድመቶችና ውሾች የተካተቱበት ነው።

ከነዚህ ውስጥ ስድስት ድመቶችና ሰባት ውሾች ተህዋሲውን ተሸክመው ተገኝተዋል።

54ቱ ደግሞ ከዚህ ቀደም ተህዋሲው ይዞ እንደለቀቃቸው የሚያሳይ የበሽታ ተከላካይ ቅንጣት ተገኝቶባቸዋል።

ዶ/ር ኤልስ ብሮንስ በኡትሬች ዩኒቨርስቲ ተመራማሪና መምህር ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ኮቪድ ያለባቸው ሰዎች ከድመትና ውሾቻቸው ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ ባያደርጉ ይመረጣል።

"እዚህ ጋ ዋናው ነጥብ የእንሰሳቱ ጤና አይደለም" ይላሉ ዶ/ር ኤልስ። ዋናው ነጥብ የቤት እንሰሳቱ "ቫይረሱን ተሸካሚና አዘዋዋሪ ከመሆናቸው ላይ ነው።"

አጥኚዎቹ ከቤት እንሰሳቱ ወደ ሰው ቫይረሱ ስለመተላለፉ በእርግጥ ያሉት ነገር ባይኖርም በውሻና በድመት ላይ ግን ተህዋሲው ጎልቶ የማይታይና እነሱም ቢሆን ምንም ዓይነት የበሽታ ምልክቶችን እንደማያሳዩ ደርሰውበታል።

ካሳዩም እጅግ ዝቅተኛ የሆኑ ምልክቶቹን ብቻ ነው የሚሆነው።

በጥናቱ የተሳተፉ ተመራማሪዎች በርካታ የቤት እንሰሳት ቫይረሱን ያገኙት ከሰው ልጆች እንደሆነና ነገር ግን በተቃራኒው እንዳልሆነ ገምተዋል።

የቤት እንሰሳቱ ባለቤቶች ተህዋሲውን ከድመትና ከውሻ የማግኘታቸው ዕድል ዜሮ ነው ልንል አንችልም፤ ነገር ግን ይህ የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ነው ብለዋል የእንሰሳት ሐኪምና የማይክሮባዮሎጂካል ዳያግኖስቲክ ሴንተር ባልደረባ ዶ/ር ብራውንስ።

በሩሲያ የእንሰሳት ሐኪሞች ለቤት እንሰሳት የተህዋሲውን ክትባት መውጋት መጀመራቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ዶ/ር ብራውን ግን ይህን ማድረጉ ጥቅሙ አልታይ ብሏቸዋል።

"ለጊዜው እንሰሳቱ ተህዋሲውን ወደ ሰው ስለማስተላለፋቸው አስተማማኝ የሆነ ሳይንሳዊ መረጃ አላገኘንም" ይላሉ።