ባልደረባቸው የተከሰሰባቸው የአሜሪካ ፖሊስ አባላት በአንድ ላይ ሥራ ለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካዋ የፖርትላንድ ከተማ አድማ በታኝ ፖሊሶች አንድ ባልደረባቸው ጥቃት ፈጽሟል ተብሎ በመከሰሱ ምክንያት ሥራቸውን ለቀቁ።
ክሱ የመጣው ባለፈው ዓመት በተከማዋ ውስጥ ተከስቶ ከባድ ቀውስ ፈጥሮ ከነበረውና ኃይል ከተቀላቀለበት የፀረ ዘረኝነት የተቃውሞ ሰልፍ ጋር ተያይዞ ነው።
ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ላይ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በተከሰተው ተቃውሞ ወቅት ክስ የተመሰረተበት የፖሊስ መኮንን "ከሕግ ውጪና ከተገቢው በላይ ኃይል ተጠቅሟል" በማለት ነው የከሰሰው።
የፖርትላንድ ከተማ የፖሊሶች ማኅበር ግን ክሱን ለመመስረት የተደረሰውን ውሳኔ "የፖለቲካ ዓላማ ያለው ነው" ሲል ተቃውሞታል።
ሥራቸውን የተለቀቁት ፖሊሶች ያሉበት የአድማ በታኝ ፖሊስ 'ፈጥኖ ደራሽ ቡድን' በሚባል የሚታወቅ ሲሆን፤ 50 አባላት አሉት።
አባላቱ ቡድኑ ውስጥ የሚያገለግሉት በበጎ ፈቃደኝነት ሲሆን ብጥብጥ ሲያጋጥም፣ ሰፊ ቦታን የሚሸፍን ፍተሻ ሲደረግና አደጋ ሲከሰት የሚሰማሩ ናቸው።
የፖርትላንድ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ የፈጥኖ ደራሽ ቡድኑ አባላት "በበጎ ፈቃደኝነት የሚያገለግሉበትን ሥራ የለቀቁ ሲሆን ከዚህ በኋላ ቡድኑ አይኖርም" በማለት፤ ነገር ግን ፖሊሶቹ በምድብ ቦታቸው ላይ ብቻ ሥራቸውን ይቀጥላሉ ብሏል።
ባለፈው ዓመት በፖርትላንድ ከተማ ሚኔሶታ ውስጥ ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ ከተገደለ በኋላ መጠነ ሰፊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ከባድ የንበረት ውድመት ሲያጋጥም ይህ የፈጥኖ ደራሽ የፖሊሶች ቡድን ረብሻውን ለመቆጣጠር ተሰማርቶ ነበር።
የፖርትላንድ ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ቡድን አባል የሆነው ኮሪ በድዎርዝ ከረብሻው ጋር በተያያዘ የቀረበበትን የወንጀል ክስ አንድ የዳኞች ቡድን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከተመለከተ በኋላ በፖሊስ መኮንንኑ ላይ ክስ እንዲመሰረት ወስኗል።
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው በረብሻው ወቅት የተቀረጸ አንድ ቪዲዮ ኮሪ በድዎርዝ በተቃውሞው የተሳተፈች አንዲት ሴትን በዱላው ገፍቶ ሲጥላትና ፊቷን በዱላው ሲጫናት ያሳያል ብሏል።
የፖርትላንድ ፖሊሶች ማኅበር ግን ክስ የተመሰረተበት አባሉ "አጀንዳ ባላቸው የከተማዋ መሪዎችና ፖለቲካዊ መልክ በተሰጠው የወንጀል ፍትህ ሥርዓት መካከል ለመስዋዕትነት እንዲቀርብ ተደርጓል" ሲል ክሱን ተቃውሞታል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የፖሊስ ማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዳሪየል ተርነር ለከተማዋ ከንቲባና ለፖሊስ አዛዡ በጻፉት ደብዳቤ ላይ "በበጎ ፈቃደኝነት በፍጥኖ ደራሽ ቡድኑ ውስጥ ለሚያገለግሉት የፖሊስ አባላት በይፋ ወጥተው ድጋፋቸውን እንዲገልጹ" ጠይቀው ነበር።
ጨምረውም የፈጥኖ ደራሽ ቡድኑ በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል የተሰማሩት "በሚቀጣጠሉና በሚፈነዱ ነገሮች፣ በድንጋይና በጠርሙስ ለመመታት እዲሁም ሌሎች አጸያፊ ፈሳሾች እንዲደፋባቸው አይደለም" በማለት በምሬት በፖሊስ ቡድኑ ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት በደብዳቤያቸው ላይ ገልጸውት ነበር።
ሁሉም የፈጥኖ ደራሽ ቡድኑ አባላትም ባልደረባቸው የሚከላከለው ሳይኖር ክስ ስለተመሰረተበት ከዚህ በኋላ አገልግሎት እንደማይሰጡ አሳውቀው ቡድኑን ለቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images















