በአሜሪካ ካሊፎርኒያ የመንግሥት ሕንጻ ላይ በተከፈተ ተኩስ አራት ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታትሟል
በአሜሪካ ደቡባዊ ካሊፎርኒያ በመንግሥት ሕንጻ ላይ በተከፈተ ተኩስ አንድ ሕጻንን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
ፖሊስ ተኩስ የከፈተውን ተጠርጣሪ አቁስሎ መያዙንና ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዱን ገልጿል።
በአሁን ሰዓት ሁኔታው "በቁጥጥር ስር" እንደዋለ የተገለፀ ሲሆን ለኅብረተሰቡ የሚያሰጋ ነገር የለም ተብሏል።
የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን በተኩሱ ምክንያት ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውን ዘግበዋል።
የካሊፎርኒያ ገዢ ጋቪን ኒውሶም በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ "አስፈሪ እና ልብ የሚሰብር" ሲሉ ሁኔታውን ገልፀውታል።
"በዚህ አሳዛኝ ክስተት ለተጎዱ ቤተሰቦች የተሰማንን ሐዘን መግለጽ እንወዳለን" ሲሉም አክለዋል።
በመጋቢት ወር አሜሪካ እንዲህ አይነት ሁለት ጥቃቶች አጋጥመዋታል።
በአትላንታ፣ ጆርጂያ አብዛኞቹ እስያዊ አሜሪካዊ የሆኑ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ፣ 10 ሰዎች ደግሞ በኮሎራዶ የሸቀጣሸቀጥ መደብር ውስጥ ተገድለዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጦር መሳሪያ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቃል የገቡ ሲሆን ምክር ቤቱም መሳሪያ የሚሸምቱ ሰዎች በዘፈቀደ እንዳይታጠቁ ለማድረግ የሚያስችል ሕግ እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል።












