ቤላሩስ በቁጥጥር ስር ያዋለችውን ጋዜጠኛ በአንድ ዝግጅት ላይ አሳየች

ሮማንና የቤላሩስ ባለስልጣናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አውሮፕላን አስገድዳ በማሳረፍ በቁጥጥር ስር አውላዋለች የተባለችውን ጋዜጠኛ ቤላሩስ በቅርቡ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለሪፖርተሮች አሳይታዋለች።

በመዲናዋ ሚንስክ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በእስር ላይ ያለው ሮማን ፕሮታሴቪች የቀረበ ሲሆን ባለስልጣናቱም አውሮፕላን ተገዶ አቅጣጫ እንዲቀይር ተደርጓል ስለተባለበት ሁኔታ ዝርዝር ተናግረዋል።

በመግለጫው ላይ የነበረ የቢቢሲ ጋዜጠኛ የ26 አመቱ ሮማን በጭንቀት ላይ እንደሆነ ሁኔታዎች ያሳብቁበት ነበር ብሏል።

በአውሮፕላኑ ውሰጥ ቦንብ አለ በሚል አውሮፕላኑ ከሚበርበት አቅጣጫ እንዲቀይርና በሚንስክ እንዲያርፍ የተደረገ ሲሆን በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ጋዜጠኛው ሮማንና እጮኛው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

አውሮፕላኑ ተገዶ ነው ያረፈው የሚለውን ጉዳይ ቤላሩስ አትቀበለውም።

በሚንስክ በሚገኘው ኬጂቢ ማረሚያ ቤት ታስሮ የሚገኘው ጋዜጠኛው ሮማን ምንም አይነት ድብደባ እንዳልተፈፀመበትና በአሁኑም ወቅት የጤንነቱ ሁኔታም ጥሩ እንደሆነ ተናግሯል።

አክሎም በቤላሩስ ላይ ጥፋት እንደፈፀመና እሱንም ለማስተካከል እንደሚሰራ አስታውቋል።

ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት ቢያዝ የሞት ቅጣት እንደሚጠብቀው በመናገር ለህይወቴ እፈራለሁ ሲል ነበር።

ሮማን በቤላሩስ በአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት አንዱ ነው። ሆኖም በአገሪቱ ውሰጥ አለመረጋጋትን በመፍጠር በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ረዘም ያለ የእስራት እድሜ ይጠብቀዋል።

ሰኞ እለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ የምርመራ ኃላፊ ዲምትሪ ጎራ ሩሲያዊቷ የሮማን እጮኛም በአገሪቱ ውስጥ መበጣበጥና ጥላቻ በማነሳሳት እንደተከሰሰች አስታውቀዋል።

እሷም ከእጮኛዋ ጋር በኬጂቢ እስር ቤት ትገኛለች።

ከአቴንስ ቪሊኒየስ እየበረረ የነበረው አውሮፕላን አቅጣጫ መቀየር የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያንን አስቆጥቷል።

በምላሹም የአገሪቱን አየር መንገድ ቤላቪያን በአየር ማረፊያቸው እንዳያርፍ እንዲሁም አየር መንገዶች የቤላሩስን የበረራ ቀጠና እንዳይጠቀሙ ማዕቀብ ጥለዋል።

ምንም እንኳን ምዕራባውያንም ሆነ ገለልተኛ አካላት አውሮፐላኑ አቅጣጫ ቀይሮ እንዲያርፍ ተገዷል ቢሉም የቤላሩስ አየር ኃይል ኃላፊ ኢጎር ጎሉብ በመግለጫው ወቅት እንደተናገሩት "ምንም አይነት አቅጣጫ ማስቀየርም ሆነ አስገድዶ ማሳረፍ አልነበረም" ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 1994 ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉትና ጨቋኝ የሚባሉት አሌክሳንደር ሉካሻንኮ ተጭበርብሯል በተባለው የነሐሴ ምርጫ አሸንፌያለሁ ከማለት በተጨማሪ በርካታ ተቃዋሚዎቻቸውን ለአስር ዳርገዋል።