የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በናይጄሪያ ከመንገድ ወጥቶ እንደነበር ተገለጸ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 777 አቃ ጫኝ አውሮፕላኖች መካከል አንዱ

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 777 አቃ ጫኝ አውሮፕላኖች መካከል አንዱ
ታትሟል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ የበረራ ቁጥር ኢቲ 3905 አውሮፕላን ናይጄሪያ ሌጎስ ደርሶ ካረፈ በኋላ ወደ መቆሚያ ስፍራው እየሄደ ሳለ ከመንገዱ ወጥቶ እንደነበር ተገለጸ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳደረጋገጠው ወደ ካርጎ የተቀየረው የመንገደኞች ቦይንግ 777-300 ግዙፍ አውሮፕላን ካጋጠመው ከስተት በኋላ ወደ ሥራ ተመልሷል።

አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ወደ ናይጄሪያዋ ሌጎስ ጭነት ይዞ ከበረረ በኋላ በሌጎስ አየረ ማረፊያ አርፎ ወደ መቆሚያው እየሄደ ሳለ የአውሮፕላኑ በስተግራ በኩል ያለው ጎማ ከአስፓልቱ መውጣቱን አየር መንገዱ አስታውቋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምስል የአውሮፕላኑ በስተግራ በኩል ያለው ጎማ ጭቃ ውስጥ ገብቶ አሳይቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ክስተቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ አውሮፕላኑ ምንም አይነት ጉዳት ሳያጋጥመው በመብረር ወደ አዲስ አበባ መመለሱን አስታውቋል። አየር መንደጉ የሌጎስ አየር ማረፊያ ሠራተኞች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናውን አቀርቧል ብሏል።

አውሮፕላኑ ከአስፓልቱ እንዲወጣ ያደረገው ምክንያት ምን እንደሆነ በአየር መንገዱ መግለጫ ላይ አልተመለከተም።

'ፍላይትግሎባል' የተባለ ድረ-ገጽ ክስተቱ ባጋጠመበት ወቅት በአየር ማረፊያው የነበረው የሜትሮሎጂ መረጃ ምንም አይነት አስቸጋሪ የአየር ጠባይ መኖሩን አላሳየም ብሏል።

በርካታ አየር መንገዶች የዓለም አቀፉን የኮቪድ-19 ስርጭት ተከትሎ ለኪሳራ ሲጋለጡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ስኬታማ ሆኖ መቀጠሉ በተደጋጋሚ ተገልጿል።

በቫይረሱ ስርጭት ምክንያት የመንገደኞች ቁጥር መቀነሱን ተከትሎ አየር መንገዱ በርካታ የመንገደኞች አውሮፕላኖቹን ወደ እቃ ጫንነት መቀየሩን ሲገልጽ ቆይቷል።