የጉግል አካታችነት ኃላፊ በአይሁድ ጠል ጽሑፉ ከሥራ ተባረረ

ጉግል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የጉግል አካታችነት ኃላፊ የነበረው ካማው ቦብ አይሁዳውያንን የሚያንቋሽሽ ጽሑፍ በማኅበራዊ ሚዲያ በመለጠፉ ከሥራ ተባረረ።

ኃላፊው ጽሑፉን የለጠፈው እአአ በ2007 ሲሆን፤ አይሁዳውያን "የጦርነት እና የግድያ ሱስ አለባቸው" ነበር ያለው።

የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭትን አስመልክቶ ከዓመታት በፊት የለጠፈው ጽሑፍ በዚህ ሳምንት ዳግመኛ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ተሰራጭቷል።

ጽሑፉ አሁን ከገጹ ጠፍቷል።

ጉግል የአካታችነት ክፍልን የከፈተው ተቋሙ እንዲሁም አገልግሎቱ በዘር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት መድልዎ እንዳያሳይ ነው። ሆኖም ግን ይህ ክፍል ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣትና አካታችነትን ባለማረጋገጥ ይተቻል።

የጉግል ቃል አቀባይ ለቢቢሲ "ከዚህ በኋላ በጉግል አካታችነት ቡድን ውስጥ አይሠራም" ብለዋል።

"የአካታችነት ሠራተኛችን ከዚህ ቀደም የጻፈው የአይሁድ ማኅበረሰብን የሚያስቀይም ጽሑፍን በጽኑ እናወግዛለን" ሲሉም አክለዋል።

ጽሑፉ ክብረ ነክ እንደሆነ የቀድሞው አካታችነት ኃላፊ እንዳመነና ይቅርታ እንደጠየቀም ተገልጿል።

ቃል አቀባዩ "ይህ ጹሑፍ የታየው ፀረ አይሁድ ጥቃቶች በዝተው አሳሳቢ በሆኑበት ወቅት ነው" በማለት፤ አይሁዳውያንን የሚያጥላላ ማንኛውንም ድርጊት እንደማይታገሱ አስረድተዋል።

ካማው ጉግልን የተቀላቀለው እአአ በ2018 ነበር። ስለ ጽሑፉ የጉግልን ሠራተኞች ይቅርታ ጠይቋል።

ጽሑፉ ምን ይላል?

በ2007 የተለጠፈው ጽሑፍ 'አይሁዳዊ ብሆን' ይሰኛል። ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል እንደዘገበውም አይሁዳውያን ስለ እስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት ምን ሊሰማቸው እንደሚገባ ያትታል።

"አይሁዳዊ ብሆን ኖሮ ራሴን በመከላከል ስም ለጦርነት እና ለግድያ ያለኝ ሱስ ያሰጋኝ ነበር። ራስን መከላከል ተፈጥሯዊ ቢሆንም ለሌሎች ስቃይ ግድ ማጣቴና ጨካኝነቴ ያሳስበኝ ነበር" ይላል።

ጽሑፉ ሰሞኑን ዳግመኛ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ የመብት ተሟጋቾች ኃላፊው ከሥራ እንዲነሳ ጠይቀዋል።

ስታንድ ዊዝ አስ የተሰኘው የእስራኤል ጉዳዮች አቀንቃኝ ቡድን ኃላፊ ማይክል ዲከንሰን "ጽሑፉ በጣም በአስቀያሚ ሁኔታ የአይሁዳውያንን ብቸኛ አገር ከናዚ ጋር ያነጻጽራል" ሲሉ ትዊት አድርገዋል።

ካማው በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም፤ ለጉግል አይሁዳዊ ሠራተኞች "ጽሑፌ መላው የአይሁድ ማኅበረሰብን የሚያጥላላ ነው። አንድ ወታደራዊ እርምጃን ለመኮነን የተጻፈው ጽሑፍ መላው አይሁዳውያንን አስቀይሟል። ለችግሩ [የእስራኤልና ፍልስጤም ጉዳይ] ቀላል መፍትሔ ያለ አይመስለኝም። የተናገርኩት ነገር ብዙዎችን ጎድቷል" ሲል ይቅርታ መጠየቁን ኒው ዮርክ ፖስት ዘግቧል።