ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተመድ በወታደሮች ቁጥጥር ስር የሚገኙት የማሊ ፐሬዚዳንት ባስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥሪ አቀረበ
የማሊ መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ፕሬዝደንት ባህ ንዳዋና ጠቅላይ ሚኒስተር ሞክታር ኦዋኔ በቁጥጥር ስር አዋለ መባሉን ተከትሎ በሀገሪቱ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጀት ተልዕኮ መሪዎቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።
ተልዕኮው በፈረንሳኛ ቋንቋ በትዊተር አማካኝነት ባቀረበው ጥሪ የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ማሊ ነገሮችን "እንድታረጋጋ"ም ጠይቋል።
ይህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥሪ የሀገሪቱ የሽግግር መንግስት ጊዜያዊ ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር በዋና ከተማዋ አቅራቢያ በሚኝ ወታደራዊ ካምፕ መወሰዳቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።
የመከላከያ ሚንስትሩም በወታደሩ ቁጥጥር ስር እንደዋሉም ተዘግቧል።
ታዲያ ይህ ድርጊት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሀገሪቱ ሁለተኛ መፈንቅለ መንግስት እንዳያስከትል ስጋት ጭሯል።
ትላንት - ሰኞ የጊዜያዊ መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኤ ኤፍ ፒ የዜና ተቋም በስልክ ወታደሮች "ሊይዟቸው መምጣታቸውን" ተናግረው ነበር ታዲያ ሀሳባቸውን ሳይቆጩ ስልኩ መቋረጡንም ነው ኤ ኤፍ ፒ የዘገበው።
የአፍሪካ ህብረት፣ የሰሜን አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ፣ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካም ድርጊቱን አውግዘው ፖለቲከኞቹ ያለቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱም ጠይቀዋል።
የመሪዎቹ እስር የተሰማው የሀገሪቱ መንግስት በባለፈው መፈንቅለ መንግስት የተሳተፉ ሁለት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ላይ የስልጣን ሽግሽግ ማድረጉ ከታወቀ ከአንድ ሰዓት በኋላ ነው።
ከ ዘጠኝ ወራት በፊትም በተደረገ መፈንቅለ መንግስት በስልጣን የነበሩት ፕሬዝዳንት ከተነሱ በኋላ ማሊ መረጋጋት ርቋት ነበር።