እውቋ አሜሪካዊት አሪያና ግራንዴና ዶልተን ጎሜዝ 'አነስ ባለ' ሰርግ ተሞሸሩ

የፎቶው ባለመብት, Ariana Grande/Instagram
ታትሟል
አሜሪካዊቷ አቀንቃኝና ተዋናይት አሪያና ግራንዴና ከእጮኛዋ ዶልተን ጎሜዝ ጋር "በጣም የቅርብ ሰዎች ብቻ በተገኙበት አነስተኛ" የሰርግ ስነ ስርዓት ተሞሽረዋል።
ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ የ27 ዓመቷ ድምጻዊቷ ስትሞሸር ታዳሚዎቹ 20 ሰዎች ብቻ እንደነበሩ ነው የተዘገበው።
በታህሳስ ወር ግራንዴ በሁለት ዓመት ከሚያንሳትና በሎሳንጀለስ የሪል ኢስቴት ወኪል ከሆነው የ25 ዓመቱ ዶልተን ጎሜዝ 'እጮኛዬ ሆኗል' ስትል ይፋ ያደረገችው።
ታዲያ ጥቂት ታዳሚያንን የያዘው ሰርግ በካሊፎርኒያ በሚገኘው በድምጻዊቷ መኖሪያ ቤት ነበር የተካሄደው።
የድምጻዊቷ ተወካይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት "ጥንዶቹ ተጋብተዋል። ሰርጉ አነስተኛና ከ20 የማይበልጥ የቅርብ ሰዎችን ያሳተፈ ነበር" ብለዋል።
"ክፍሉ በፍቅርና በደስታ የተሞላ ነበር"ም ብለዋል።
ጥንዶቹ የተሞሽሩበትን የደቡባዊ የካሊፎርኒያ አከባቢ በቅርቡ መነጋገሪያ የነበረው የእንግሊዙ መስፍን የሚኖርበትም ነው።
የድምጻዊቷ ባለቤት ጎሜዝ በደቡባዊ ካሊፍርኒያ ያደገ ሲሆን ለ5 ዓመታት በቅንጡ ሪል ኢስቴት ሽያጭ ላይ የሚሰራ መሆኑ ተገልጾል።
ጥንዶቹ ከጋብቻ በፊት ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጌዜ በፍቅር ቆይተው ነው ትዳር የመሰረቱት።












