ኮሮናቫይረስ፡ በሕንድ የኮቪድ ቀውስ ያፌዘችው ቻይና ውግዘት እየገጠማት ነው

የፎቶው ባለመብት, SINA Weibo
ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር ግንኙነት አለው የተባለ አንድ የማህበራዊ ሚዲያ በኮሮናቫይረስ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ሕንድ ላይ በማፌዙ ውዝግብ አስነስቷል።
በቻይው የማህበራዊ ሚዲያ ዌቦ ላይ የተለጠፈው ፎቶ፤ ቻይና ሮኬት ስታስወነጭፍ የተፈጠረውን እሳት በሕንድ ውስጥ በኮቪድ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች አስከሬን ከሚቃጠልበት እሳት ጋር ጎን ለጎን እያጻጸረ ያሳያል።
"የቻይና እሳት እና የሕንድ እሳት" የሚል ጽሑፍም ተካቶበታል።
ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ይፋ የተደረገው መረጃ ብዙም ሳይቆይ ተሰርዟል።
በይፋዊው የቻይና የሕግ አስከባሪ ኤጀንሲ ገጽ ላይ መስፈሩ ታውቋል። ኤጀንሲው በቻይና ኮሚኒስት ማዕከላዊ ፓርቲ የፖለቲካና የሕግ ጉዳዮች ኮሚሽን ስር ሲገኝ በአገሪቱ ታዋቂ የማህበራዊ ሚዲያ ዌቦ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች አሉት።
መረጃው ቢሰረዝም ፎቶውን ያስቀሩት ተጠቃሚዎች ጉዳዩ "ተገቢ ያልሆነ" እና ቻይና "ለሕንድ ርህራሄ ልታሳይ እንደሚገባ" ጽፈዋል።
የቻይናው ግሎባል ታይምስ ዋና አዘጋጅ ሁ ዢጂን "በዚህ ወቅት የሰብዓዊነት ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርጋችሁ ለሕንድ ርህራሄን በማሳየት የቻይና ህብረተሰብን በሥነ ምግባር ከፍታ ላይ አኑሩ" ሲል ጽፏል።
የዌቦው መልዕክት በሕንድ እየተጠናከረ የመጣውን የኮቪድ-19 ቀውስ አስመልክቶ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ለሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የሃዘን መግለጫ ከላኩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው የወጣው።
ቻይና ከሕንድ ጋር ያላትን ትብብር ከፍ ለማድረግ እና አስፈላጊ ሲሆን ማንኛውንም ተጨማሪ እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኗንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ሕንድ በሁለተኛው ዙር የኮቪድ ማዕበል እየተናጠች ነው። ሆስፒታሎቿ ሥር በሰደደ የአልጋ እና ኦክስጅን እጥረት ውስጥ ይገኛሉ።
ትላንት እሑድ ብቻ 3,689 ሞት አስመዝግባለች። ይህም ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ቀን በርካታ ሰዎች ሲሞቱ ይህ ከፍተኛው ነው።
ይህ የሆነው አገሪቱ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ400ሺህ በላይ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በማስመዝገብ የመጀመሪያዋ አገር ከሆነች ከአንድ ቀን በኋላ ነው።












