አሜሪካ በአፍጋኒስታን ያሉ ወታደሮቿን ማስወጣት ጀመረች

አሜሪካ አፍጋኒስታን ያሉ ወታደሮቿን በይፋ ማስወጣት መጀመሯ ተገለጸ።
አሜሪካ ወታደሮቿን ማስወጣት የጀመረችው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “ የዘላለም ጦርነት” ያሉት ግጭት ማብቂያን ተከትሎ ነው።
አሜሪካና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) ለ20 ዓመታት ያህል በአፍጋኒስታን ቆይተዋል።
እስከ መስከረም 11 ድረስ የሚቀጥለው ወታደሮቹን የማስወጣት እቅዱ ተግባራዊ እየሆነ ያለው ግጭቶች በተባባሱበትና የአፍጋኒስታን ኃይሎች የበቀል ጥቃቶችን ለመመከት በተጠንቀቅ ባሉበት ወቅት ነው።
ታሊባን ከአሁን በኋላ ዓለም አቀፍ ወታደሮችን ኢላማ ላለማድረግ በስምምነቱ እንደማይገዛ አስጠንቅቋል።
ባለፈው ዓመት በፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕና በታጣቂዎቹ መካከል በተደረገ ስምምነት፤ የታሊባን ወታደሮች ዓለም አቀፍ ወታደሮች ላይ ጥቃት መሰንዘር ሲያቆም፤ የውጭ ኃይሎቹ በፈረንጆቹ ግንቦት አንድ ይወጣሉ ተብሎ ነበር።
በወቅቱ ባለሥልጣናት፤ የታሊባን ወታደሮች የምዕራብ ወታደራዊ ካምፕን ከአማጺያኑ እስላማዊ ቡድን እየጠበቁ እንደሆነ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ነገረ ግን ይህ የታሊባን ወታደሮች በአፍጋኒስታን ኃይልና በንጹኃን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት አላገደውም።
የአሜሪካ ጦር ጀነራል ስኮት ሚለር ወታደሮቹ እየወጡ እንደሆነ በመግለፅ የውጪ ኃይሎች ላይ ጥቃት እንዳይፈፀም አስጠንቅቀዋል።
“ስህተት እንዳትሰሩ! በጥምረቱ እና የአፍጋኒስታን የጸጥታ ኃይልን የሚደግፈው ጦር ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ጥቃት በኃይል አጸፋ ለመውሰድ ወታደራዊ አማራጭ አለን” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው በተጋራ ቪዲዮ ላይ ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ባለፈው ወር ወታደሮቹን በፈረንጆቹ ግንቦት 1 ለማስወጣት የተያዘውን እቅድ የተወሰኑ ወታደሮች እስከተያዘው ዓመት መስከረም 11 ድረስ ይቆያሉ ሲሉ ገፍተውት ነበር።
ምክንያታቸው ደግሞ መስከረም 11 በፔንታጎን ላይ የደረሰው ጥቃት 20ኛ ዓመት በመሆኑ ለጸጥታው ሁኔታ ጥሩ አይሆንም የሚል ነበር።
የታሊባን ቃል አቀባይ ግን “ መመሪያን መጣስ ለታሊባኖች ማንኛውንም የአጸፋ ጥቃት ለመፈፀም በር ይከፍታል” ብለዋል።
ይሁን እንጂ የታሊባን ታጣቂዎች ጥቃት ከማድረሳቸው በፊት ከመሪዎቻቸው የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
አንዳንድ የዘርፉ ተንታኞች በበኩላቸው አሜሪካ ወታደሮቿን ለማስወጣት ያስቀመጠችው ቀነ ገደብ ከተተገበረ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት ሊቀሰቀስ ይችላል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ወታደሮቿን ለማስወጣት የሎጂስቲክስ ተግዳሮት ገጥሟታል።
ኤፒ እንደዘገበው ጦሩ ጓዙን እየሸከፈ ሲሆን በአፍጋኒስታን ገበያ የሚሸጣቸውንና ይዟቸው የሚሄዳቸውን ነገሮች ለመወሰን እያሰበ ነው።
አሜሪካ ባለፉት 20 ዓመታት በአፍጋኒስታን ብቻ በርካታ ሚሊየን ዶላሮችን ፈሰስ ያደረገች ሲሆን በአጠቃላይ ደግሞ ከ2 ሺ በላይ ወታደሮቿ ተገድለውባታል።












