ማንቸስተር ዩናይትድ ሮማን 'ሲረመርም' አርሰናል ተሸንፏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብሩኖ ፈርናንዴዝና ኤዲሰን ካቫኒ እያንዳንዳቸው 2 ጎሎችን በማስቆጠር በትናንትው ምሽት የዩናይትድ ድልን አድምቀውት አምሽተዋል።
በአውሮፓ ሊግ አሊያም እነሱ እንደሚሉት በዩሮፓ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ በታዋቂው ኦልድ ትራሮፍርድ የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድና የጣሊያኑ ሮማ ሐሙስ ምሽት ተፋልመዋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ 6 ለ 2 ሮማን 'ረምርሟል'።
በጨዋታው ዩናይትዶች በብሩኖ ፈርናንዴዝ አማካይነት በጨዋታ መባቻ ቅድሚያ ቢያገኙም ሮማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ጎሎችን አከታትለው አስቆጥረዋል።
የበረኛው ሳጥን ውስጥ ፖል ፖግባ ኳስ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሎሬንዞ ፔሌግሪኒ ሲያስቆጥር የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ኤዲን ዤኮ ደግሞ ሁለተኛውን አስቆጥሮ ነው ቡድኖቹ እረፍት የወጡት።
ነገር ግን ማንቸስተር ዩናይትድ አፈር ልሶ በመንሳት በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን ቀልብሶታል።
ኡራጋያዊው ጉምቱ አጥቂ ኤዲሰን ካቫኒ ከእረፍት መልስ ባስቆጠራት ጎል ዩናይትድ አቻ ሆነ። በዚህ ያልተመለሰው ካቫኒ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ በረኛው የመለሳትን ኳስ አግኝቶ እንደገና ከመረብ ዶላት።
የአሠልጣኝ ኦሌ ጉናር ሶልሻዬር ልጆች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሮማ ጎል እንዲያስቆጥርባቸው አልፈቀዱም።
ምንም እንኳ ዩናይትድ ያገኘው ፍፁም ቅጣት ምት ዕድለኛ የሚያስብለው ቢሆንም ክሪስ ስሞሊንግ የሠራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘችውን 'ሪጎሬ' ፈርናንዴዝ ወደ ጎል ከመቀየር ያገደው አልነበረም።
በስተመጨረሻ ታዳጊው ግሪንውድ ከካቫኒ የተሻገረችለትን ኳስ በቀኝ እግሩ ወደ መረብ በመላክ ስድስተኛዋን ጎል አስቆጥሯል።
ቀጥሎ ደግሞ ፈረንሳዊው ፖል ፖግባ ከፈረናንዴዝ የተሻመለትን ኳስ በጭንቅላቱ ከመረብ አዋህዷታል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በአውሮፓ ከፍተኛ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ስድስት ጎል በማስቆጠር ታሪክ ፅፈዋል።
ዩናይትድ በአውሮፓ ጨዋታ ሮማ ላይ በርካታ ጎል ሲያዘንብ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በአውሮፓ ቻምፒዬንስ ሊግ በ2007 በተገናኙ ወቅትም ጎል እንደ በረዶ ወርዶ ነበር።
የአሁኑ አሠልጣኝ ሶልሻዬር ተቀያሪ በነበረት ጨዋታ ዩናይትድ ሮማን 7ለ 1 ነበር የረታው።
ኦሌ ምናልባት ዋንጫ ማንሳት የሚችል ከሆነ 'ልምድ የለውም'፤ 'ዋንጫ መብላት አይችልም' ሲሉ የሚሞግቱ ተቺዎቹን አፍ ሊዘጋ ይችላል።
ዩናይትድ ወደ ፍፃሜው የሚያደርገውን ጉዞ ያሳመረ ይመስላል። ተንታኞች ለዩናይት በቀጣዩ ወር የፍፃሜ ጨዋታ አስጊ ሊሆን የሚችለው አንድ ነገር የተከላካይ መስመሩ ነው ይላሉ።
ምንም እንኳ የዩናይትድ ተከላካይ መስመር ባለፉት ስድስት የአውሮፓ ሊግ ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ ቢቆጠርበትም ከሮማ ጋር በነበረው ጨዋታ ግን ሁለት ጎል አስተናግዷል።
ከጨዋታው በኋላ አስተያየት የሰጠው ኦሌ "መልካም ውጤት ነው ግን ሥራችን አልተጠናቀቀም" ሲል ተደምጧል።
በሌላኛው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ አርሰናል በቪያሪያል 2 ለ 1 ተሸንፏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ጎሎች የተቆጠሩበት አርሰናል በሁለተኛው አጋማሽ በተገኘች ፍፁም ቅጣት ምት ተስፋ የምትሰጥ አንድ ጎል አስቆጥሮ ወደ መቀመጫው ለንደን ተመልሷል።
የግማሽ ፍፃሜ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ቀጣይ ሳምንት ሐሙስ ይከናወናሉ።
















