ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርጫ 2013፡ የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ ምርጫው በስድስት ወር እንዲራዘም ጠየቀ
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተቀመጠውን መስፈርት አላሟሉም ተብለው ፈቃዳቸው ከተሰረዙ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የገዳ ፓርቲ መጪው ብሔራዊ ምርጫ በስድስት ወር እንዲራዘም ጠየቀ።
የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ-ገዳ ቢሊሱማ ከምርጫ ቦርድ ጋር በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲያካሄድ በነበረው ክርክር ፈቃዱ መሰረዙ ትክክል እንዳልሆነ እንደተወሰነለት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ሮበሌ ታደሰ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ሮበሌ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክርክር ሲያደርግ መቆየታቸውን እና ጠቅላይ ፍርድ ቤትም መሰረዙ ትክክል አይደለም ሲል መወሰኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
"በምርጫ ቦርድ ምክንያት ከምርጫ ውጪ ሆነናል" የሚሉት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ሮበሌ፣ መጪው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በስድስት ወር ተራዝሞ መስከረም 2014 ዓ.ም እንዲካሄድ ለቦርዱ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የፓርቲያቸው ስም ከገዳ ፓርቲ የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ-ገዳ ቢሊሱማ በሚል መቀየራቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የምርጫ ደንብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ስርዓት ቁጥር 1162/2011 መሰረት በማድረግ በአገሪቱ በምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዋጁ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ድጋሚ ምዝገባ እንዲያከናውኑ መደረጉ ይታወሳል።
ቦርዱም በአዋጁ የተቀመጠውን መስፈርት አላሟሉም በማለት ግንቦት ወር 2012 ዓ.ም መሰረዛቸውን ካስታወቃቸው ፓርቲዎች መካከል የገዳ ሥርዓት ፓርቲ አንዱ ነበር።
"የፓርቲው የመስራቾች መረጃ አልተሟላም በሚል ሰበብ ነው ፓርቲያችን እንዲሰረዝ የተደረገው፤ ይህንኑ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተናግረን ነበር፤ ይኹን እንጂ በምርጫ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት አንድ በክልል ደረጃ የሚወዳደር ፓርቲ 4000 የመስራቾች ፊርማ ማቅረብ የሚጠበቅበት ቢሆንም እኛ ግን የ6845 አባላት ፊርማ አቅርበን ነበር፤ የትኛውንም ሕግ ሳንተላለፍ እና መረጃ እያለን ነው የሰረዙብን" በማለት አቶ ሮበሌ ይናገራሉ።
ከዚያም ጉዳዩን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማመልከታቸውን እና ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ክርክር ካካሄዱ በኋላ፣ ፓርቲው የተሰረዘበት አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ ፍርድ ቤቱ እንደወሰነላቸው አቶ ሮበሌ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱም ለምርጫ ቦርድ ለፓርቲው የመከላከል ወይንም ደግሞ መልስ የመስጠት እድል ከሰጠው በኋላ ፓርቲው ይቀጥል ወይንም ይሰረዝ የሚለውን ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ለቦርዱ ኃላፊነት ሰጥቶ ነበር ሲሉም ያስረዳሉ።
ነገር ግን "ጉዳያችን ወደ ምርጫ ቦርድ መመለስ የለበትም፤ ፍርድ ቤቱ ራሱ ፍትሃዊ የሆነ ውሳኔ ይስጠን በማለት ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመለከትን" በማለት ሂደቱን አብራርተዋል።
ምርጫ ቦርድም 'ፓርቲው መሰረዝ አለበት' በሚለው አቋሙ በመጽናት ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረቡን ይናገራሉ።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን የምርጫ ቦርድን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ የፓርቲውን አቤቱታ መስማቱንና ውሳኔውን ለምርጫ ቦርድ ማስገባቱን አቶ ሮበሌ ገልጸዋል።
አቶ ሮበሌ ፓርቲው የቦርዱን ውሳኔ እየጠበቀ መሆኑንም ተናግረዋል።
የገዳ ሥርዓት ፓርቲ ማን ነው?
የገዳ ሥርዓት ፓርቲ በ1995 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ባለፉት ሦስት አገራዊ ምርጫዎች ተሳትፈዋል።
በ1997 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ፓርቲው በኦሮሚያ ምክር ቤት መቀመጫ አግኝቶ እንደነበር አቶ ሮበሌ ያስታውሳሉ።
"ዓላማችን የገዳ ሥርዓት መገንባት ነው" የሚሉት አቶ ሮበሌ ታደሰ፤ በገዳ ሥርዓት መሰረት ምርጫ በየአራት ዓመቱ እንዲካሄድና ሥልጣን በስምንት ዓመቱ እንዲገደብ ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ፓርቲያቸው የኦሮሚያ ክልል በፌዴሬሽን ሥርዓት ኢትዮጵያ ደግሞ በኮንፌዴሬሽን መዋቀር አለባት የሚል ፕሮግራም እንዳለው ይናገራሉ።