ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
'እናቱን ገድሎ የበላው' ግለሰብ በስፔን ፍርድ ቤት ቀረበ
እናቱን ገድሎ ሰውነቷን በመቁረጥ እና አስከሬኗን በመብላት ወንጀል የተጠረጠረው ግለሰብ በስፔን ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡
የጓደኛቸውን ስጋት ተከትሎ ወደ 66 ዓመቷ እናቱ ቤት ያቀናው ፖሊስ አልበርቶ ሳንቼዝ ጎሜዝን በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 በቁጥጥር ስር አውሎታል፡፡
ፖሊስ በቤቱ ውስጥ የሰውነት አካል ክፍሎች ተበታትነው ማግኘቱን ተናግሯል። አንዳንዶቹ በፕላስቲክ የዕቃ መያዣ ውስጥ ተገኝተዋል፡፡
ተከሳሹ እናቱን መቆራረጡንና መብላቱን እንደማያስታውሰው ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
ከመታሰሩ በፊት በስብዕና መታወክ እና በአደንዛዥ እጽ ሱስ ይሰቃይ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በእናቱ ማሪያ ሶሌዳድ ጎሜዝ ላይ ከዚህ ቀደም ያደረሳቸው ጥቃቶች በፖሊስ ይታወቅ እንደነበር እና በተያዘበት ወቅትም እናቱ ጋር እንዳይደርስ የተላለፈበትን የዕግድ ትእዛዝ መጣሱን የስፔን ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የካቲት 2019 ምስራቅ ማድሪድ ውስጥ በሚገኘው ቤት ውስጥ አስፈሪ ትዕይንት ፖሊስ ማየቱን አድምጧል፡፡
የተወሰኑት የሰውነት ክፍሎች እየበሰሉ የነበሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በቀጣይ ለመጠቀም እንዲሆኑ መከማቸታቸውን ኤል ሙንዶ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
በወቅቱ 26 ዓመቱ የነበረው ተከሳሹ እናቱን አንቆ መግደሉን አምኖ አንዳንድ ጊዜ ስጋዋን መብላቱን አንዳንዴም ለውሻ ሰጥቻለሁ ብሏል ተብሏል።
የፍርድ ሂደቱ እንደቀጠለ ነው።