ሕፃናት ፕሌቶን ከተሰኘው የመሮጫ ማሽን እንዲርቁ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

ታትሟል

የአሜሪካ የደህንነት ተቆጣጣሪ ድርጅት ሰዎች ፕሌቶን የተሰኘው የመሮጫ ማሽን መጠቀም እንዲያቆሙ አሳሰበ።

ኮንሲዩመር ፕሮዳክት ሴፍቲ የተሰኘው የመንግሥት ተቆጣጣሪ ድርጅት ፕሌቶን በተባለው የመሮጫ ማሽን ሳቢያ 39 አደጋዎች ደርሰዋል የሚል መግለጫ ለቋል።

ድርጅቱ እንዳለው በማሽኑ ሳቢያ አንድ ሰው ሕይወቱ አልፏል።

ፕሌቶን የተባለው የመሮጫ ማሽን አምራች ድርጅት ባለፈው ወር አንድ ሰው መሞቱን አረጋግጦ ሕፃናት ወደ ማሽኑ እንዳይጠጉ አሳስቧል።

ነገር ግን የጥራት ተቆጣጣሪው ድርጅት ያወጣው መግለጫ "ከእውነት የረቀና አሳሳች ነው" ሲል አጣጥሎታል።

ፕሌቶን ቤት ውስጥ የሚተከሉ ብስክሌቶችና መሮጫ ማሽኖች አምራች ድርጅት ሲሆን ማሽኖቹ ላይ በተገጠመ ቴክኖሎጂ አማካይነት ሰዎች ስክሪን ላይ በሚታይ አስተማሪ እየተመሩ ስፖርት መሥራት ይችላል።

በኮሮናቫይረስ አማካይነት ሰዎች ወደ ስፖርት ቤቶች መሄድ አለመቻላቸውን ተከትሎ የድርጅቱ ማሽኖች ሽያጭ እጅግ ከፍ ብሎ ነበር።

ተቆጣጣሪ ድርጅቱ "አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ" ሲል ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ አንድ ሕፃን ወደ ማሽኑ ተጎትቶ ሲገባ የሚያሳይ ምስል ለቋል።

መግለጫው እንደሚለው ማሽኑ "ለሕፃናት እስከሞት የሚያደርስ ከፍተኛ አደጋ ይጋርጣል።"

የዕቃዎች ጥራት ተቆጣጣሪው ድርጅት ከ39 አደጋዎች መካከል አንዱ የተከሰተው አንድ ወላጅ ማሽኑ ላይ እየሮጡ ሳለ ነው ይላል።

ወላጆች ማሽኑን ሲጠቀሙ በአቅራቢያቸው ሕፃናት ባይኖሩ ይመረጣል ይላል ተቆጣጣሪው ድርጅት።

አዋቂ ሰዎች ፕሌቶን የመሮጫ ማሽኖችን ሲጠቀሙ በተዘጋ ክፍሎች ውስጥ ቢሆን ይመረጣል ሲል ድርጅቱ መክሯል።

ፕሌቶን ግን አሁንም "ማሽኖቼ ለመጠቀም ምቹና ደህንነታቸው የተጠበቀ ነው። የደህንነት መመሪያዎችም ተካተውበታል" ይላል ባወጣው መግለጫ።

ነገር ግን ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት፣ የቤት እንስሳትና አንዳንድ ዕቃዎች ከማሸኖቹ እንዲርቁ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።