በኒጀር ትምህርት ቤት ውስጥ በተቀሰቀሰ እሳት 'ማምለጫ' ያጡ ቢያንስ 20 ህፃናት ህይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Tchima Illa Issoufou/BBC
በኒጀሯ ርዕሰ መዲና ኒያሚ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ በተነሳው እሳት ምክንያት ትምህርት ላይ የነበሩና 'ማምለጫ' ያጡ በትንሹ 20 ተማሪዎች መሞታቸው ተዘገበ።
እሳቱ ባለፈው ማክሰኞ ቀትር ላይ ሲቀሰቀስ ህፃናቱ በሳር በተሰራ ክፍል ውስጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ነበር።
የትምህርት ቤቱ በር በእሳቱ ነበልባል በመዘጋቱ ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ተማሪዎች በአጥር ዘለው ለማምለጥ መገዳቸውን የመምህራን ማኅበሩን አስተዳደሮች ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
ሆኖም ትምህርት ላይ የነበሩ የቅድመ መደበኛ ህፃናት ተማሪዎች ይህን ማድረግ ባለመቻላቸው ለህልፈት ተዳርገዋል።
የእሳት ሲሳይ የሆነው ትምህርት ቤት በመንግስት የሚተዳደርና በኒያሚ 'ፓይስ ባስ' በተሰኘ ወረዳ የሚገኝ የቅድመ መደበኛና የታዳጊዎች መደበኛ ትምህርት የሚሰጥበት ሲሆን ከሳርና ጡብ የተሰሩ ክፍሎችን ቀላቅሎ የያዘ መሆኑን በከተማው የምትኘው የቢቢሲ ዘገቢ ገልፃለች።
በቃጠሎ 28 የሳር ክፍሎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውንና ሌሎች ክፍሎች ላይም ጉዳት መድረሱንም ጠቁማለች።
የመማሪያ ክፍል እጥረትን ለማቀለል የሳር ክፍሎቹ መሰራታቸውንም ዘገባቢዋ ገልፃለች።
በአደጋው የ6 ዓመት ልጁን ያጣው አባት መንግስት ለህፃናት ደህንነቱ የተጠበቀ የመማሪያ ክፍል እንዲገነባ አሳስቧል።
"ሁሉንም ነገር በፈጣሪ እጅ መተው የልብንም፣ ሁሉንም ነገር በወጣው ይውጣ ብለን መተው የለብንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ሰከንድ ሳይሞላ 20 ልጆችን አጣን። መንግስት በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ከሳር የተሰሩ የመማሪያ ክፍሎችን እንዲያስወግድ ማሳሰብ አለብን"ም ብለዋል።
የሀገሪቱ እሳት መከላከል አገልግሎት አዛዥ በብሄራዊ ጣቢያ ቀርበው የአደጋ መከላከል ሰራተኞች ስፍራው ላይ በፍጥነት ቢደርሱም " እሳቱን ግን ሀይለኛ ነበር" ማለታቸው ተሰምቷል።












