የ20 ዓመቱን ጥቁር አሜሪካዊ የተኮሰችበት ፖሊስ በግድያ ወንጀል ተከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሚኒሶታ አንድ ጥቁር አሽከርካሪን በጥይት የገደለችው ነጭ የቀድሞ የፖሊስ መኮንን በሁለተኛ ደረጃ የመግደል ወንጀል ክስ እንደተመሠረተባት ዐቃቤ ሕግ ገለጸ፡፡
ኪም ፖተር በቁጥጥር ስር የዋለች ቢሆንም በኋላ ግን በ 100,000 ዶላር ዋስ ተለቃለች፡፡
ፖተር በስህተት ማደንዘዣ መስሏት ሽጉጧን በመምዘዝ ዳውንት ራይት ላይ መተኮሷን ፖሊስ ገለጿል፡፡
የራይት ቤተሰብ ጠበቃ ቤን ክራምፕ በበኩላቸው ግድያው "ሆን ተብሎ እና ህገ-ወጥ የኃይል እርምጃ በመጠቀም የተፈጸመ ነው" ብለዋል፡፡
ክስተቱን ተከትሎ ኪም ፖተርም እና የአከባቢው የፖሊስ አዛዥ ቲም ጋኖን ሥራቸውን ለቀዋል፡፡
ግድያው በሚኒያፖሊስ አቅራቢያ በምትገኘው በብሩክሊን ሴንተር በፖሊስ እና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭቶችን ቀስቅሷል።
ረቡዕ ረፋድ ላይ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የተጣለውን የሰዓት እላፊ ገደብን በመተላለፍ ከፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ውጭ ተሰብስበዋል፡፡
ተቃዋሚዎች ጠርሙሶችን እና ሌሎች ዕቃዎችን በፖሊስ ላይ ሲወረወሩ ፖሊስም አስለቃሽ ጭስ እና አስለቃስ ጋዝ በመጠቀም ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የአፍሪካ አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድን በመግደል በተከሰሰው ነጭ የቀድሞው የፖሊስ መኮንን የፍርድ ሂደት ምክንያት በሚኒያፖሊስ ውጥረቱ ከፍ ብሎ ነበር።
የሚኒሶታ የወንጀል ጉዳዮች ቢሮ እንዳስታወቀው ፖተር ረቡዕ ጠዋት በቁጥጥር ስር ውላለች፡፡ ዋስትናው ከመቀዱ በፊት በሁለተኛ ደረጃ ግድያ በመጠርጠር ወደ ሄነፒን ካውንቲ እስር ቤት አምርታለች፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜም ሐሙስ ፍርድ ቤት ትቀርባለች፡፡
በክሱ መሠረት ከፍተኛው ቅጣት የ 10 ዓመት እስራት እና የ20,000 ዶላር ቅጣት ነው፡፡
ዓቃቤ ህጎች ፖተር "ቸልተኛ" እንደነበረች እና በድርጊቷም "ምክንያታዊ ያልሆነ እርምጃ" እንደወሰደች ማሳየት አለባቸው ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የብሩክሊን ሴንተር ከንቲባ ማይክ ኤሊዮት ሰዎች በሠላማዊ መንገድ እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
"እንደ ከተማም ሆነ እንደ አመራር ያለን ተግባር ትክክለኛ የሆኑ ድምጾች እንዲሰሙ መፍቀድ እንዲሁም እንደ ህብረተሰብ መረጋጋታችንን እና ጥንካሬያችንን ለማደስ እና ወደፊት የሚወስደንን መንገድ መፍጠር ነው" ብለዋል፡፡
ቤተሰቡ ምን አሉ?
የቤተሰቡ ጠበቃ ክራም በሰጡት መግለጫ "የትኛውም የጥፋተኝነት ውሳኔ ለራይት ቤተሰቦች የሚወዱትን ሊመልስላቸው አይችልም" ብለዋል፡፡
"የ 26 ዓመቷ የቀድሞ ፖሊስ በመሳሪያ መካከል ያለውን ልዩነት ታውቃለች፡፡ ኪም ፖተር በትንሽ የትራፊክ ጥሰት እና በጥፋተኝነት ማዘዣ ምክንያት ዳውንትን ገደላለች" ብለዋል፡፡
የራይት እና ፍሎይድ ቤተሰቦች ማክሰኞ ዕለት ተሰባስበው ያልታጠቁ ጥቁር አሜሪካውያን በፖሊስ የሚደርስባቸው ግድያ እንዲቆም ጠይቀዋል።
የፍሎይድ ወንድም ፊሎኒስ ፍሎይድ "ሌላ አፍሪካ-አሜሪካዊ ሰው ሲገደል ዓለም ተጎድቷል" ብሏል፡፡
ሰኞ ዕለት የፖሊስ አዛዡ ጋኖን እንዳሉት የአንድ ዓመት ወንድ ልጅ ነበረው ራይት በቀድሞ የፖሊስ ባልደረባዋ ፖተር ማደንዘዣ ለማውጣት በማሰብ በስህተት ሽጉጧን መዛ ተጠቅማለች ብለዋል፡፡
ቤተሰቦቹ ግን ይህን አይቀበሉትም፡፡
የራይት አክስት የሆኑት ናይሻ "ያንን ቪዲዮ ሁሉም ሰው እንዳየው እኔም ተመልክቼዋልሁ። ሴትየዋ ጠመንጃዋን ረዘም ላለ ጊዜ ይዛው ነበር" ብላለች፡፡
ተኩሱ አንዴት ተከሰተ?
ዳውንት ራይት በመኪናው ታርጋ ላይ ጊዜው ያለፈበት መለያ በመያዙ ከመኪናው እንዲወርድ ተደረገ፡፡ ቤተሰቦቹ ግን በዘር ምክንያት ተለይቶ ተይዟል ይላሉ፡፡
የፖሊስ ልብስ ላይ በተገጠመው ካሜራ መሠረት ራይት ቀደም ሲል የወጣበት የመያዣ ወረቀት እንዳለበት ሲገልጹለት ከፖሊሶች ሲሸሽ ያሳያል።
ራይት እንደገና ወደ መኪናው ከገባ በኋላ እና ፖተር ከመተኮሳቸው በፊት በተደጋጋሚ "ቴዘር (ማደንዘዣ) ላወጣ ነው ሲሉ ተደምጠዋል ፡፡
የራይት እናት ልጃቸው ከተያዘ በኋላ እንደደወለላት ለጋዜጠኞች ገልጸው የኢንሹራንስ ዝርዝሮችን ለፖሊስ በስልክ እንደሰጠች አስታውቀዋል፡፡
ከተሽከርካሪው እንዲወጣ ፖሊስ ሲያዝዘው እንደሰማች ተናግረዋል፡፡ የግጭት ድምፅ የነበረ ሲሆን አንድ መኮንን ስልኩን ዘግቶ እንዲወርድም ነግሮታል፡፡
በድጋሚ መልሳ ስትደውልለት ፍቅረኛው መመታቱት ለእናቱ ነገረች፡፡
"ስልኩን ወደ ሹፌሩ ወንበር ስታዞር ልጄ እዛው ላይ ተጋድሟል፤ ምላሽም አልሰጠም" ብላለች እያለቀሰች፡፡
"ልጄን ያየሁበት የመጨረሻው አጋጣሚም ነበር" ብላለች።












