በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ሥራ ያቆመው ሰዓት በሌላ መንቀጥቀጥ ሥራ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፈረንጆቹ 2011 ጃፓንን በመታት የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት መሥራት አቁሞ የነበረው የ100 ዕድሜ ያለው የጃፓን የግድግዳ ሰዓት ሥራ ጀምሯል።
በአንድ የቡድሂስት ቤተ-እምነት ውስጥ የተሰቀለው ይህ የግድግዳ ሰዓት የጃፓንን ሰሜን ምስራቅ ክፍል በመታው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ነው ሥራ አቁሞ የነበረው።
በወቅቱ የመሬት መንቀጥቀጡ ባስነሳው ሱናሚ ምክንያት ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
የሰዓቱ ባለቤት ቡንሹን ሳካኖ ሰዓቱ እንደገና እንዲቆጥር ለማድረግ ለዓመታት ቢታገሉም አልተሳካላቸውም።
ነገር ግን ከ10 ዓመት በኋላ ሌላ አነስተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲያጋጥም ሰዓቱ ድጋሚ ሥራ ጀምሯል።
በጃፓኗ ሚያጊ ግዛት ያማማቶ ውስጥ ካለ አንድ ቤተ-እምነት ውስጥ ተሰቅሎ የሚገኘው ሰዓት ሥራ ጀምሯል ሲል አንድ ጋዜጣ አስነብቧል።
ሚያጊ የተሰኘው የጃፓን ክልልና ፉኩሺማ ክፉኛ በመሬት መንቀጥቀጡ ከተመቱ ክፍሎች መካከል ነበሩ።
መጋቢት 2011 [በፈረንጆቹ] ሱናሚው ጃፓን ሲንጥ ነው ይህ ቤተ-እምነት የፈራረሰው።
ቤተ-እምነቱ ከባህር ዳርቻው ጥቂት መቶ ሜትሮች ርቆ የሚገኝ ሲሆን በሱናሚው ምክንያት ሲፈራርስ ነው ሰዓቱ ሥራ ያቆመው።
ጃፓን የሱናሚውን 10ኛ ዓመት ካከበረች ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በሌላ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመታለች።
ሳይንቲስቶች በዚህ ዓመት የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ10 ዓመት በፊት ያጋጠመው መሬት መንቀጥቀጥ ትራፊ ነው ብለው ያምናሉ።
የዘንድሮው መሬት መንቀጥቀጥ በተከሰተ በበነጋው የሰዓቱ ባለቤት የሆኑት ሳካኖ ቀና ብለው ሲመለከቱ ሰዓታቸው መቁጠር ጀምሯል።
ይኸው ሰዓቱ አሁን እያንቃጨለ ሁለት ወራት አልፈውታል።
80 ሴንቲሜትር ስፋት ያለውን ይህን የግድግዳ ሰዓት አቶ ሳካኖ የገዙት የ2011 ሱናሚ ጃፓንን ከመምታቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ነበር።
ሰዓቱ በተፈጠረው መሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ተነቃንቆ ሥራ ሳይጀምር እንዳልቀረ ብዙዎች ይገምታሉ።
የቤተ-እምነቱ አገልጋይ የሆኑት ሳካኖ ጃፓንን ከናጣት መሬት መንቀጥቀጥ በኋላ ቤተ-እምነቱን ለበጎ ፈቃደኞች እንደ ቢሮ ሆኖ እንዲያገለግል ፈቅደዋል።
የ58 ዓመቱ ሳካኖ ሰዓታቸው ድጋሚ መቁጠር በመጀመሩ ደስታ እንደተሰማቸው አልሸሸጉም።












