ደጋፊዎቹ የማድሪድን መኪና ያጠቁት ሊቨርፑል ከቻምፒየንስ ሊግ ተሰናበተ

ሞ ሳላህ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የአምናው ባለድል ሊቨርፑል ከተወዳጁ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር በሪያል ማድሪድ ተሸንፎ ተሰናብቷል።

የስፔኑ ቡድን ማድሪድና ሊቨርፑል በአንፊልድ ያደረጉት ጨዋታ ያለምንም ግብ ቢያጠናቀቅም በመጀመሪያው ዙር ፍልሚያ ማድሪድ በማሸነፉ ወደ ቀጣይ ዙር አልፏል።

ማድሪድ ፖርቶን አሸንፎ ወደ ሩብ ፍፃሜው ያለፈው ቼልሲን ይገጥማል።

የሊቨርፑል ተጫዋቾች በመጀመሪያው አጋማሽ ወርቃማ ዕድሎችን ወደ ጎል መቀየር ተስኗቸው አምሽቷል።

ግብፃዊው ሞሐመድ ሳላህ ያገኛትን ኳስ ወደ ጎል ቢሞክርም የሪያል ማድሪዱ ግብ ጠባቂ ኮርትዋ መልሶበታል።

የማድሪዱ ግብ ጠባቂ ኮርትዋ፤ የሊቨርፑሉ አምበል ጄምስ ሚልነር የሞከራትን ሙከራም በመጀመሪያ አጋማሽ ማዳን ችሏል።

ሌሎችም የሊቨርፑል ተጨዋቾች ወደ ጎል ሊቀየሩ የሚችሉ አጋጣሚዎችን ሲያባክኑ አምሽተዋል።

አቻ ለመሆን የሁለት ጎል ዕዳ ይዞ የገባው ሊቨርፑል በርካታ የጎል ማግባት ሙከራዎችን ቢያደርግም የዚነዲን ዚዳን ልጆችን ማስደንገጥ አልቻለም።

የስፔኑ ማድሪድ ሊቨርፑልን በአጠቃላይ ውጤት 3-1 መርታቱን ተከትሎ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈ ሲሆን ከቶማስ ቱኸል ቼልሲ ጋር ይፋለማል።

የሊቨርፑል ድክመት

የሊቨርፑል ተጨዋቾች በታሪካቸው ታሪክን በመቀልበስ ቢታወቁም የዩርገን ክሎፕ ልጆች ግን ይህን ማድረግ አልቻሉም።

ተንታኞች ሊቨርፑሎች ወደ ቀጣዩ ዙር ላለማለፉ ተጠያቂ ሊያደርጉ የሚገባው ራሳቸውን ነው ይላሉ።

ለወትሮው ኳስ ከመረብ ጋር ካላዋኻደ የማይመለሰው ሞሐመድ ሳላህ በትላንትናው ጨዋታ ሁለት ወሳኝ ኳሶችን አባክኗል።

የሞሐመድ ሳላህ ኳሶች መረብ አለመንካታቸው አስደንቆ ሳያበቃ ሌሎችም የሊቨርፑል ተጨዋቾች ሲስቱ አምሽተዋል።

ምንም እንኳ ሊቨርፑል 90 ደቂቃ ሙሉ ጎል አስቆጥሮ ሪያል ማድሪድ ላይ ጫና በመፍጠር የተሻለ ውጤት ለማግኘት ቢጥሩም በርካታ ድክመት ታይቶባቸዋል።

ሰዓቱ በገፋ ቁጥር የሪያል ማድሪድ ተጫዋቾች በራስ መተማመን ከፍ እያለ ሲመጣ ታይቷል።

ዩርገን ክሎፕ ዲዮጎ ጆታንና ቲያጎ አልካንታራን ቀይረው ቢያስገቡም ተጨዋቾቹ ለውጥ ሊያመጡ አልቻሉም።

400 የሚሆኑ የክለቡ ደጋፊዎች ከአንፊልድ ውጭ ሆነው ቡድናቸውን ለመደገፍ ተሰባስበው ነበር።

ነገር ግን ቡድናቸውን ከመደገፍ ይልቅ የሪያል ማድሪድ ተጫዋቾችን አሳፍሮ የመጣውን አውቶቡስ መስታወት ሰብረዋል።

ሊቨርፑል የእግር ኳስ ክለብ በዚህ ድርጊት በተጫዋቾቹ ስም ሪያል ማድሪድን ይቅርታ ጠይቋል። የመርሲሳይድ ፖሊስ ደግሞ ምርመራ አደርጋለሁ ብሏል።

በሌላ ጨዋታ የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ የጀርመኑን ቦሩሲያ ዶርትመንድ 2-1 [በጠቅላላ ውጤት 4-2] በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

በቀጣዩ ዙር የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች ማድሪድ ከቼልሲ፤ ማንቸስተር ሲቲ ከፒኤስጂ ይፋለማሉ።