የወደፊቱ የአርሰናል አምበል ይሆናል የተባለለት ቡካዮ ሳካ ለምን የተለየ ሆነ?

ታትሟል

ቡካዮ ሳካ በተማረበት ግሪንፊልድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእሱ ሥራዎች የኩራት ምንጭ ናቸው።

በትምህርት ቤቱ የእንግዳ መቀበያ አካባቢ በሚገኘው ግድግዳ ላይ ቡካዮ ሳካ የፈረመበት አርሰናል እግር ኳስ ክለብ መለያ ተሰቅሏል። ከስሩ ደግሞ የ19 ዓመቱ እግር ኳሰኛ "አመሰግናለሁ" የሚል ጽሁፍ አስፍሯል።

በትምህርት ቤቱ የሚገኙ ተማሪዎችም ሆነ አስተማሪዎች ስለ ቡካዮ ሳካ ሲያወሩ በኩራት ሲሆን አሁንም ድረስ የወሬ ርዕስ ሆኖ እንደቀጠለ ነው።

"ሳካ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ሲመረጥ ሁሉም ሰው በጣም ተገርሞ ነበር'' ይላል የሳካ የቀድሞ የሰውነት ማጎልመሻ መምህርና ምክትል አሰልጣኝ ማርክ ሃርቪ።

"በእድሜ ከፍ የሚሉት ተማሪዎች የእሱን ህይወት በሚገባ ይከታተላሉ። ሁሌም ቢሆን እሱ የሆነ ነገር ሲያደርግ፣ ግብ ሲያስቆጥር አልያም ለጎል አመቻችቶ ሲያቀብል በትምህርት ቤቱ የዋትስአፕ ቡድን ላይ ሁሉም ሰው የሚያጋረው እሱን ነው። እንደውም ትንንሾቹ ተማሪዎች እሱ በትምህርት ቤታችን ይማር እንደነበር አያምኑም" የሚለው ደግሞ የሳካ የቀድሞ አሰልጣኝ የነበረው ዲፔሽ ፓቴል ነው።

አርሰናል ሳካን ፍለጋ ወደ ትምህርት ቤቱ የመጣው የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተና ከመውሰዱ በፊት ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ ትምህርት ቤቱን ሲለቅ በፈተናው አራት ትምህርቶች ላይ ኤ አምጥቷል።

ገና በልጅነቱም በእግር ኳን ትምህርት ቤቱን ወክሎ በክልላዊና አገራዊ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል። በእሱ ምክንያትም ቡድኑ በርካታ ስኬቶችን አግኝቷል።

"በዚህ ትምህርት ቤት ለበርካታ ዓመታት ቆይቻለሁ፤ ነገር ግን ገና ከመጀመሪያው ነበር ሳካ የተለየ ችሎታ እንዳለው ያስተዋልኩት" ይላል ዲፔሽ ፓቴል። አክሎም "ሜዳ ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ ጨዋታውን የሚመለከትበት መንገድ፣ እንዲሁም የሚወስናቸው ውሳኔዎች በጣም የተለዩ ነበሩ። በጣም የሚያስገርም የቡድን ተጫዋች ነበር።''

"በትምህርት ቤታችን ቆይታው ሰባተኛው ዓመት ላይ በአንድ ውድድር ላይ ለዋንጫ አልፈን 4 ለ 3 የተሸነፍንተበትን ጨዋታ አስታውሳለሁ። በጨዋታው በርካታ የጎል እድሎችን አግኝቶ አልተጠቀመባቸውም ነበር። ከሜዳ ሲወጣ አስታውሳለው በጣም ተበሳጭቶ ነበር። ለመሸነፋችን ምክንያት እሱ እንደሆነ ነበር ያሰበው። 'ከዚህ በኋላ እግር ኳስ ደግሜ አልጫወትም' አለኝ።"

"ወደ መጨረሻው ጨዋታ ያለፈነው በቀላሉ ነበር። በአብዛኛዎቹ ጨዋታዎች አስገራሚ ብቃቱን ሲያሳይ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ለሌሎቹ ተጫዋቾች እድል ለመስጠት ስል የጨዋታው ግማሽ ላይ አቀይረው ነበር። ስምንተኛው ዓመት ላይ ግን ሁሉንም ውድድር ማሸነፍ ችለናል። በርካታ ዋንጫዎችን አንስተን ነበር። ሁሌም ቢሆን ስለቡድኑ ነበር የሚያስበው።"

የክንፍ መስመር አጥቂው ሳካ ከሰባት ዓመቱ ጀምሮ ከመድፈኞቹ ጋር የነበረ ሲሆን ለዋናው ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወተው በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ በአውሮፓ ሊግ ውድድር ነበር። በመቀጠል ደግሞ ጥር ወር ላይ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ መጫወት ችሏል።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ከአርሰናል ጋር የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። በኤምሬትስ የሚያቆየውን አዲስ ኮንትራትም ፈርሟል። ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ ከ16 ዓመት በታች ሲጫወት ከነበረበት ተነስቶ በዋናው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫወተ። በጨዋታው እንግሊዝ ዌልስን አሸንፋለች።

ምንም እንኳን ሳካ በአርሰናል ቤት የቋሚነት ቦታውን ለመረከብ እና በብሔራዊ ቡድኑ ሰአልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት ቡድን ውስጥ ሰብሮ ለመግባት ብዙ ኢዜ ባይፈጅበትም የመጣበትን ግን አልረሳም።

"ለብዙ ዓመታት የትምህርት ቤቱ ኃላፊ ከነበሩት ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት አለው። የቼልሲ ደጋፊ ከሆኑት የክፍል ኃላፊውም ጋር ቢሆን በጣም የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው'' ይላል ሃርቪ።

"በጣም ቅርብ የሆኑ ጥቂት ጓደኞች ነበሩት። ምናልባት ከአምስት እስከ ስምነት የሚሆኑ ልጆች ነበሩ። ሁሉም በጣም ጥሩ ተማሪዎች ነበሩ። ስፖርቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ትምህርት ላይም ቢሆን ጎበዞች ነበሩ።"

የሳካ የቀድሞ ክፍል ኃላፊ ከሁለት ዓመታት በፊት በጡረታ ሲገለሉ የሽኝት ዝግጅቱ ላይ ያለውን ክብር በአካል ተገኝቶ አሳይቷል።

"በሽኝት ዝግጅቱ ላይ ከአባቱ ጋር በመገኘት ለሰዓታት ያክል ቆይቶ ነው ተመለሰው። ከቀድሞ ጓደኞቹንና ከአስተማሪዎቹ ጋር ሲጫወትም ነበር" ይላል ሃርቪ። "ሁሉም ሰው ያውቀዋል። ከእንግዳ ተቀባዮቹ እስከ ጥበቃ ድረስ ሁሉም ጋር ጥሩ ግንኙነት አለው።"

ቡካዮ ሳካ ከልጅነቱ ጀምሮ ያልተለየው ነገር ቢኖር ለስኬት ያለው ከፍተኛ ፍላጎት ነው። በአርሰናልና በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ተቀናቃኞቹን የሚሸውድበትና የማይገመቱ ውሳኔዎቹ ሁሌም ልዩ ያደርጉታል።

"በጣም ዝምተኛ ልጅ ነበር። ሁሉንም ሰው የሚያከብርና በጣም ጥሩ አድማጭ ነው። ሰዎችን ለማስደሰት የሚጥርና በሁሉም ነገር ምርጥ መሆን የሚፈልግ አይነት ሰው ነው" ይላል ከ18 ዓመት በታች የቀድሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኙ ኒል ዴውስኒፕ።

"4-4-3 አሰላለፍ ተጠቅመን ስንጫወት ሁሌም በግራ ተከላካይ መስመር በኩል እንዲጫወት እንዳርገዋለን። ከሜሰን ግሪንዉድ ጋር ተመሳሳይ ቦታ ነው። ሳካ እንደ አንደ መስመር አጥቂም መጫወት ይችላል። በተጨማሪም በቀኝ በኩልም ይጫወታል። በጣም አስገራሚ ተጫዋች ነው።''

"ከኳሷ ጋርም ሆነ ያለኳስ ሩጫው በጣም ያምራል። ተጫዋቾችንም በቀላሉ ማለፍ ይችላል። ከተከላካዮች ጋር ለአንድ ሲገናኝም ኳሷን ሚገፋበት መንገድ ይለያል፤ ግብ ማስቆጠርም አይከብደውም።''

"በሁለቱም እግሮቹ መጫወት ይችላል። አጨዋወቱ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ ነው'' ይላል የአርሰናል የቀድሞ ተጫዋች መልማይ የነበረው ማርቲን ታይለር።

"ተጫዋቾችን በቀላሉ የማለፍ፣ ግብ የማስቆጠርና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ላይ በጣም ጥሩ የሆነ ችሎታ አለው። የሚያስገርመው ደግሞ እነዚህን ነገሮች የሚያደርገው ብዙም ሳይጨነቅ ነው። እንደ ቀልድ ነው የሚያደርጋቸው''

"ገና የ7 እና የ8 ዓመት ህጻን እያለ እንኳን የእግር ኳስ ችሎታውን አለማስተዋል አይቻልም። ይህን አይነት ችሎታ በትምህርት የሚገኝ አይደለም'' ይላል ሀርቪ።

''አንድ ቀን የአርሰናል አምበል ይሆናል''

የሥነልቦና ጥንካሬ እና አካላዊ ብቃት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሁሉ ተጫዋቾች የሚጠበቅ ነገር እየሆነ የመጣ ሲሆን እነዚህን ነገሮች ካሟሉ እድገታቸው ፈጣን እንደሚሆን ማርቲን ያምናል።

"ትምህርት ዋናውና ወሳኙ ነገር ነው። በተለይ ደግሞ ታዳጊ ተጫዋቾች። እነዚህ ወጣት ተጫዋቾች በርካታ የማኅበራዊ ኃላፊነት የሚጠይቁ ዝግጅቶች ላይ ይሳተፋሉ። ቡካዩ ሳካ እና ጓደኞቹ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ንግግር ሲያደርጉ በከፍተኛ ብስለትና ማስተዋል ነው።''

"ከቤተሰቦቹ እና ከአርሰናል ጋር በመሆን እድገቱን ስንከታተል ነበር። ወደ ትምህርት ቤቱ ሄጄም የቀድሞ መዝገቡን ተመልክቻለሁ። በጣም የሚያስገርም ታዳጊ ነው።''

"ሁሌም ቢሆን ሰው አክባሪ ነው። እንደ ሳካ አይነት የእግር ኳስ ብቃት ኖሮህ የቡድን አጋሮችህ እና ተቀናቃኞችህ ተመጣጣኝ ያልሆነ ብቃት ሲኖራቸው አንዳንዴም ቢሆን ከእነሱ ጋር መመሳሰል ያስፈልጋል፤ በተለይ ታዳጊ እያሉ። ይህ ወጣት ሁሉም አይነት በጎ ምግባር የሚታይበት ነው። ወደፊት የአርሰናል አምበል እንደሚሆን አስባለሁ።''

ታይለር እንደሚለው የሳካ ጠንካራ ሥነልቦናው ነው ለዚህ ሁሉ ስኬት ያበቃው። "እንደ ኦባምያንግ እና ላካዜት ካሉ ኮከብ ተጫዋቾች ጋር ነው የሚጫወተው። በእድሜም በልምድም ከሚበልጡት ተጫዋቾች ጋር ነው የሚጫወተው፤ በዚህ ታዳጊ እድሜው።"

"ሁሌም የመጀመሪያ ሀሳቡ ወደፊት መሄድ ነው። በርካታ ተጫዋቾች ይህ ችሎታ የላቸውም። እንደ ቡካዮ ሳካ አይነት በራስ መተማመን ያለው ተጨዋች ማንም ሊያስቆመው አይችልም። በእግሩ ብቻ ሳይሆን በጭንቅላቱም ነው የሚጫወተው። እንዲህ አይነት ችሎታ አብሮህ ይወለዳል እንጂ በልምድ ወይም በትምህርት አይመጣም። ምናልባት በትምህርትና በልምድ ችሎታው ሊዳብር ይችል ይሆናል እንጂ ውስጡ ያለው ብቃት ግን አብሮት የተወለደ ነው።''

በያዝነው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዓመት በጣም ምርጥ በነበረው ጨዋታው ላይ ሳውዝሃምፕተንን 3 ለ 1 ሲያሸንፉ አንድ ግብ አስቆጥሮ ሌላ ደግሞ አመቻችቶ ሰጥቷል።

"አሁንም ቢሆን ገና የእግር ኳስ ሕይወቱ ጅማሮ ላይ ነው ያለው። ምንም እንኳን በክለብም ሆነ በበብሔራዊ ቡድን አስገራሚ ጉዞ እያደረገ ቢሆንም ብዙ የሚቀሩት ነገሮች አሉ። በጣም ወጣት ታዳጊ ነው'' ይላል ዴውስኒፕ።

"በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የሚጫወት ተጫዋች ማሰልጠን ለክለብ አሰልጣኞች የማይገኝ እድል ነው። የመጫወት ፍላጎት፣ ብቃት፣ ድፍረትና ተስፋ ያለው ተጫዋች ነው።''