ጥቁር ተማሪዎችን የሚያንኳስስ መልዕክት የተለዋወጡ ተማሪዎች ተቀጡ

ታትሟል

በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት 'የባሪያ ንግድ' የተሰኘ የመልዕክት መለዋወጫ ቡድን ግሩፕ ፈጥረው የጥቁር ተማሪዎችን ዋጋ ሲገምቱ የነበሩ ተማሪዎች እንዲቀጡ ተደረገ።

'ስናፕቻት' በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መልዕክት ሲለዋወጡ የነበሩት ተማሪዎች አሌዶ ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት የሚማሩ ሲሆን አንደኛውን ጥቁር ጓደኛቸውን አንድ ዶላር ያወጣል፤ ሌላኛው ደግሞ 100 ዶላር ያወጣል የሚል መልዕክት ሲለዋወጡ እንደነበር ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

ትምህርት ቤቱ ይህንን ተከትሎ ባደረገው የሥነ ምግባር ምርመራ ተማሪዎቹ የዘረኝነትና የበይነ መረብ ትንኮሳ ፈጽመው አግኝቻለሁ ብሏል።

ነገር ግን አንዳንድ ወላጆች ትምህርት ቤቱ ተገቢውን እርምጃ አልወሰደም በሚል ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ተማሪዎቹ በስናፕቻት ላይ በነበራቸው የቡድን የመልዕክት ልውውጥ ግብርና እና ጨረታ የተሰኙ ቃላትን ይጠቀሙ ነበር ሲል ኒውዮርክ ታይምስ የዘገበ ሲሆን፤ በአንድ መልዕክት ላይ ደግሞ ተማሪዎች የተሻለ ዋጋ እንዲያወጡ የጸጉራቸው አይነት ወሳኝነት አለው ይላል።

አንድ ተማሪ ጥሩ ዋጋ እንዲያወጣ ጸጉሩ ለስላሳ መሆን አለበት እንደማለት ነው።

ትምህርት ቤቱ በበኩሉ ጉዳዩን ከፖሊስ ጋር በመሆን በቅርበት እየተከታተለው እንደሆነ በማስታወቅ በተፈጠረው ነገር በእጅጉ ማዘኑን ገልጿል።

"ባካሄድነው ምርመራ መሰረት የሥነምግባር ጥሰት እና ዘረኝነት እንዲሁም የበይነ መረብ ትንኮሳ መፈጸሙን አረጋግጠን ተገቢውን እርምጃ ወስደናል" ብሏል ትምህርት ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ።

ነገር ግን እነማን ላይ ምን አይነት እርምጃ እንደተወሰደ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

"ይህ ተግባር በርካታ ተጎጂ ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ሥነ ልቦናዊ ህመም አስከትሏል። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ተማሪዎችም ላይ ጫና አድርሷል" ይላል መግለጫው።

በአሌዶ ትምህርት ቤት ስር የሚገኘው 'ዳኒኤል ናይንዝ ግሬድ ካምፓስ' ኃላፊ የሆኑት ካሮላይን አንስሌይ እንዳሉት ምርመራው ዘረኝነት የተሞላበት ንግግር እንደነበረውና የትምህርት ቤቱንም ሆነ የግዛቲቱን ሕግ የሚጥስ መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል።

ነገር ግን አንዳንድ ወላጆች አሁንም ቢሆን ኃላፊዎች የወሰዱትን እርምጃ ከመተቸት ወደኋላ አላሉም።

"ከዘረኝነት ይልቅ የበይነ መረብ ጥቃት ብለው ነው የወሰዱት። ይሄ በጣም ያናድደኛል" ሲል ማርክ ግረብስ የተባለ ወላጅ ኤንቢሲ ለተባለው የዜና አውታር ገልጿል።

"ውስጤ በጣም ነው የሚረበሸው። እራሳቸውን እንዴት ያለ ቦታ ላይ ቢያስቀምጡ ነው ይህንን ሊያደርጉ የሚችሉት? የሆነ ሰው ላይ ይህን መሰል ተግባር ለመፈጸም ማነው መብት የሰጣቸው?" ሲል ይሄው ወላጅ በምሬት ጠይቋል።

ኤላ ቡሎክ የተባለችው ሌላኛዋ ወላጅ ደግሞ በተፈጠረው ነገር በእጅጉ እንዳዘነችና ኃላፊዎች ተማሪዎቹ የሰሩትን ነገር የጥላቻ ንግግር እንኳን ብሎ አለመጥራቱ እንዳስገረማት ገልጻለች።

"እነዚህ ተማሪዎች ያደረጉትን ነገር ለማድረግ መጀመሪያውኑ ጥቁር ተማሪዎቹን እንደ ሰው አይቆጥሯቸውም ነበር ማለት ነው። ለዚህም ነው ይሄን ሁሉ ነገር ሲለዋወጡ ለእነሱ ቀላል የነበረው" ብላለች።