ኮሮናቫይረስ፡ ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት የጆንሰን ኤንድ ጆንሰንን ክትባት አገዱ

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የጆንሰን ኤንድ ጆንሰንን ክትባት ከደም መርጋት ጋር ያለውን ቁርኝት ለመመርመር ሲባል እንዳይሰጥ መታገዱን የደቡብ አፍሪካ የጤና ሚንስትር ዝዌሊ ምኪዜ ገለጹ።

ውሳኔው "ለጥንቃቄ ሲባል የተወሰደ" እርምጃ ነው ሲሉ ዶ/ር ምኪዜ አስታውቀዋል።

ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ በጣም አነስተኛ በተባለ የደም መርጋት ሪፖርት በመደረጉ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን (ጄ ኤንድ ጄ) የኮቪድ ክትባትን ለጊዜው አግደዋል፡፡

እንደአሜሪካው የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር (ኤፍ ዲ ኤ) ከሆነ ከተሰጡት 6.8 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች ውስጥ ስድስት የደም መርጋቶች ተመዝግበዋል ሲል አስታውቋል፡፡

በአውሮፓ ህብረት በዚህ ሳምንት የተጀመረው የክትባቱን ስርጭት ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ለአፍታም ቢሆን አቁሟል፡፡

የአስትራዛኔካ ክትባት ላይም ተመሳሳይ ጉዳዮች ተከስተዋል።

ኤፍዲኤ ጊዜያዊ እገዳው "በብዙ ከመጠንቀቅ" የተነሳ መሆኑን ገልጿል፡፡ አንድ ሰው ከደም መርጋት ጋር በተያያዘ መሞቱን ያረጋገጠ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡

ስድስቱም ጉዳዮች ከ 18 እስከ 48 ዓመት ባሉ ሴቶች ላይ የተከሰተ ሲሆን ክትባቱን ከወሰዱ ከስድስት እስከ 13 ቀናት ድረስ ባሉት ጊዜዎች ምልክቶች ታይተዋል፡፡

በዚህም ሁሉም በአሜሪካ የሚገኙ የፌዴራል ጣቢያዎች ስለ ደህንነቱ ተጨማሪ ምርመራዎች እስኪጠናቀቁ ድረስ ክትባቱን መጠቀም አቁመዋል፡፡ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍም ተመሳሳይ እርመጃ ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

አሜሪካ ከ 31 ሚሊዮን በላይ የኮቪድ ህሙማንን በማስመዝገብ እና ከ 562,000 በላይ ህይወታቸው በማለፍ በዓለም ቀዳሚ ናት፡፡

ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የአሜሪካ የጤና ኩባንያ ቢሆንም ክትባቱ በዋናነት የተሠራው ቤልጅየም ውስጥ በሚገኘው የመድኃኒት ማምረቻ ቅርንጫፉ ነው። ድርጅቱ ጆንሰን ተብሎም ይጠራል፡፡

ከሌሎቹ ክትባቶች በተለየ መልኩ አንድ ጊዜ መሰጠቱ እና በመደበኛው ማቀዝቀዣ ሊከማች ስለሚችል ተመራጭ አድርጎታል፡፡

ብዙ ሀገሮች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክትባቶችን ቀድመው ቢይዙም ዕውቅና ያገኘው በጥቂት ሀገሮች ብቻ ነው፡፡

ከየካቲት 27 ጀምሮ በአሜሪካ ጥቅም ላይ እንዲውል ቢደረግም የፋይዘር-ባዮኤንቴክ እና የሞዴርና ክትባቶች በስፋት ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

በአሜሪካ ውስጥ በጄ ኤንድ ጄ ክትባት ሰባት ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች የተሰጠ ሲሆን እስከአሁን ከተሰጡት አጠቃላይ ክትባቶች ወደ ሦስት በመቶ ያህሉን ይሸፍናል፡፡

የሀገሪቱ ከፍተኛ የኮቪድ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ በበኩላቸው ፈቃዱ ስለመሰረዙ አስተያየት ለመስጠት ገና መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ ምንም ዓይነት የደም መርጋት ችግር ባይከሰትም ክትባቱን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰጠችው ደቡብ አፍሪካም ክትባቱን መስጠት ለአፍታ አቁማለች።

ከሌሎች ክትባቶች በበለጠ የደቡብ አፍሪካውን ዝርያ የመከላከል አቅም እንዳለው ጥናቶች ካመለከቱ በኋላ ክትባቱ ተመራጭ ሆኗል፡፡ ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ ወደ 300 ሺህ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች ተከትበዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ሁኔታውን እየተከታተለ መሆኑን እና ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ተቆጣጣሪዎች ሪፖርቶችን እየጠበቀ መሆኑን ለሮይተርስ ገልጿል፡፡

ክትባቱን ለአውሮፓ ህብረት አገራት ማድረስ ጀምሮ የነበረው ጄ ኤንድ ጄ በ24 ሰዓታት ውስጥም ለአውሮፓ ህብረት ማከፋፈሉን ለአፍታ ማቆሙን አስታወቀ፡፡

በአውሮፓ ህብረት ክትባቱ ባለመሰጠቱ ባለሙያዎች ቀጣዩ እርምጃቸው ምን እንደሆነ ለማየት ወደ አሜሪካ ያማትራሉ ተብሏል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ህብረትን የክትባት ዘመቻ በጣም ቀርፋፋ ሲል ተችቷል። የአሁኑ ክስተትም ተጨማሪ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡