የኦስትሪያው የጤና ሚኒስትር በከፍተኛ ድካም ምክንያት ከስልጣናቸው ለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኦስትሪያ የጤና ሚኒስትር በከፍተኛ ድካም ምክንያት ከስልጣናቸው መልቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
የ60 ዓመቱ ሩዶልፍ አንሾበር በአውሮፓውያኑ ጥር 2020 ሲሾሙ ሃገሪቱን የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ያደረገችውን ጥረት መርተዋል፡፡
"ሪፐብሊኳ [ኦስትሪያ] በአስር ዓመታት ውስጥ እጅግ በከፋ የጤና ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት 100 ፐርሰንት ብቁ የጤና ሚኒስትር ያስፈልጋታል። እኔ ደግሞ አይደለሁም" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
በሥራ ያሳለፉባቸው 15 ወራት "15 ዓመታት ያህል ተሰምቶኛል" ብለዋል፡፡ የሃገሪቱ ቻንስለር ሰባስቲያን ኩርዝ በበኩላቸው ሚኒስትሩ "ራሳቸውን ለሃገራችን መስዋዕት ያደረጉ ናቸው" ብለዋቸዋል፡፡
አንሾበርን ተክተው በጥምር መንግስቱ ውስጥ የሚገኙት ሐኪሙ እና እንደሳቸው የአረንጓዴ ፓርቲ አባል የሆኑት ዎልፍጋንግ ሙክስቴይን ተሰይመዋል።
ቀደም ሲል መምህር የነበሩት አንሾበር ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች "ከመጠን በላይ ሠርቻለሁ እናም ደክሞኛል" ብለዋል፡፡
የደም ግፊት፣ የደም ዝውውር እና ስኳር ህመምን ጨምሮ በበርካታ የጤና ችግሮች ሲሰቃዩ እንደነበርም አብራርተዋል፡፡
"በወረርሽኝ ወቅት ማንም ከስህተት የፀዳ አይደለም። ስህተቶች ቢኖሩም እዚህ ሃገር በትክክለኛው መንገድ የተከናወኑ ብዙ ነገሮች እንዳሉ እምነት አለኝ" ሲሉ የመንግስታቸውን ሚና ተከላክለዋል፡፡
የኦስትሪያው ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ቫን ደር ቤለን በበኩላቸው አንሾበርን "በሪፐብሊኳ ስም እና በግላቸውም በዚህ እጅግ በጣም አስቸጋሪ እና አስጨናቂ በሆነ የወረርሽኝ ወቅት በመሥራታቸው አመስግነዋል፡፡"
ቻንስለር ኩርዝ በበኩላቸው የሚኒስትሩ ከስልጣን ለመልቀቅ መወሰን ወረርሽኙ በግለሰብ ላይ ብቻ "ቀን ከሌሊት ውሳኔዎችን በሚሰጡ" ባለስልጣናት ላይም ተጽዕኖ እንዳለው ማሳያ ነው ብለዋል ፡፡












