ኮሮረናቫይረስ፡ የማዳጋስካር ምክር ቤት አባላት የኮቪድ-19 ክትባትን ለማግኘት ወደ ሌላ አገራት እየሄዱ ነው

ታትሟል

የማዳጋስካር የሕዝብ እንደራሴዎች የኮቪድ-19 ክትባትን ከአገራቸው ውጪ ለመከተብ እየሞከሩ ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ሲቴኒ ራንድሪያናሶሎንያኮ ስሙን ባልጠቀሱት አገር ክትባት መውሰዳቸውን በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ አስፍረዋል።

ሌላኛው የምክር ቤት አባል ሴን ኢውጊና ቮኒናሂትሲ ወደ ፈረንሳይ ቤተሰባቸውን ለመጠየቅ በሚሄዱበት ወቅት ክትባቱን እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

ይህ የሆነው ማዳጋስካር ለዓለም አቀፉ የክትባት ትብብር ኮቫክስ እንደምትመዘገብ ካስታወቀች በኋላ ነው።

የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ከጥቂት ወራት በኋላ በሽታውን ለማከም ያስችላል ያለችውን ባሕላዊ መድኃኒት ያስተዋወቀችው ማደጋስካር ክትባት እንደማያስፈልጋት ገልጻ ነበር።

ኮቫክስ የተባለውና ለበርካታ አገራት የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለማቅረብ ከሚሰራው ጥምረት የአገራት ዝርዝር ውስጥ ባለመግባቷ ክትባቱን ሳታገኝ ቆይታለች።

ማዳጋስካር ኮቪድ-ኦርጋኒክስ የተባለውን ባሕላዊ መድኃኒት በፕሬዝዳንቷ አማካይነት ስታስተዋውቅ የቆየች ሲሆን መድኃኒቱ ወደ ሌሎች አገራትም እንደተላከ ተዘግቦ ነበር።

ነገር ግን የመድኃኒቱ ምንነትና ያስገኘውን ውጤት በሚመለከት በጤና ባለሙያዎች የተባለ ነገር የለም።

ይህ ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠ መድኃኒት በሻይ እና በክኒን መልክ ተዘጋጅቶ የኮቪድ-19 ፈዋሽ መድኃኒት ተብሎ ሲተዋወቅ ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት ግን እስካሁን ድረስ ለኮሮረናቫይረስ ምንም ዓይነት ፈዋሽ መድኃኒት አለመገኘቱን ሲያስታውቅ ቆይቷል።

ማዳጋስካር የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተቀብለው ሕዝባቸውን እየከተቡት ያለውን የወረርሽኙን መከላከያ ክትባት በኮቫክስ በኩል ለማግኘት ጥያቄ አቅርባለች።

የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ፕሮፌሰር ጃን ልዊስ ራኮቶቮ እንዳሉት ክትባቱን ለማግኘት የተለያዩ ደረጃዎችን ማለፍ አለበት ለዚህ ደግሞ ምዝገባን መፈጸም ዋነኛው እርምጃ ነው ሲሉ የክትባት አቅርቦት ጥምረት ከሆነው ኮቫክስ ውስጥ ለመግባት ማዳጋስካር እያደረገች ያለውን ገልጸዋል።

የማደጋስካሩ ፕሬዝደንት አንድሬ ራጆሊን ኮቪድ-19ን ይፈውሳል በማለት ሲያስተዋውቁት የነበረው 'መድኃኒት' በስፋት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በማዳጋስካር እስካሁን ከ24 ሺህ 400 በላይ ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው የታወቀ ሲሆን 418 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሰበብ ለሞት ተዳርገዋል።