ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በ10 ሳንቲም ሲሸጥ የነበረ መጽሔት ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ አወጣ
ቆየት ያለው የቀልድ ይዘት ያለው እና ሱፐር ማንን ያስተዋወቀ ነው የተባለው ህትመት ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ ነው ተሸጠ።
በ3.25 ሚሊዮን ዶላር [ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ] የተሸጠው ይህ አስቂኝ ይዘት ያለው መጽሔት ከመደበኛ ሰው የላቀ ኃይል ያለው ገፀባህሪን (ሱፐርማን) ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀ ነው ተብሏል።
ታዲያ የመገኘት ዕድሉ ጠባብ እንደሆነ የተነገረለት ይህ ዕትም የተሸጠበት ዋጋ ክብረ ወሰን ነው።
'አክሽን ኮሚክ' ቁጥር 1 የሚል ርዕስ ያለው ህትመቱ፣ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1938 ሲወጣ የመሸጫ ዋጋው 10 ሳንቲም ነበር። ታዲያ አሁን ላይ የተሸጠበት ዋጋ መጽሔቱን በዓለም ውዱ ቀልድ አዘል ህትመት አድርጎታል።
የሱፐር ማንን አነሳስ የሚያትተው ህትመቱ የዚህ ዓይነት ዘውግን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀ እንደሆነ ይታመናል።
አሁን ላይ የ 'አክሽን ኮሚክ' ቁጥር 1 ህትመት 100 የሚሆኑ ዕትሞች እንዳሉ ይገመታል።
እናም ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ የተሸጠው ይህ ዕትም "የ1930ዎቹ የፊልም መጽሔቶች ስብስብ ውስጥ ስር ተሰውሮ" መገኘቱን መጽሔቱን በበይነ መረብ ላይ ለጨረታ ያቀረበው ኮሚክ ኮኔክት የተባለ ተቋም ገልጿል።
"በእርግጥ ከመደበኛ ሰው የላቀን ገፀባህሪ የያዘ ዘውግ የተጀመረበት ነው" የሚለው የተቋሙ ባለድርሻና ጨረታውን ያሰናዳው ቪንሰንት ዙርዞሎ፣ ይህ መጽሔት በዘመኑ በሺዎች የሚቆጠር ዕትም ነበረውም ብሏል።
ህትመቱን እጁ ካስገባ ከሦስት ዓመታት በኋላ ማንነቱ ላልታወቀ ሰው የሸጠው ተቋሙ 1 ሚሊዮን ዶላር አትርፎበታል።