ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩናይትድ ኪንግደም የምያንማር አምባሳደር እና ሠራተኞቻቸው ወደ ኤምባሲያቸው እንዳይገቡ ተከለከሉ
ለንደን የሚገኙት የምያንማር አምባሳደር ወደ ኤምባሲው ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ መደረጋቸውን ገለፁ።
አምባሳደሩ ኪያው ዝዋር ሚን እምዳሉት የምያንማር ወታደራዊ አታሼ የኤምባሲውን ሠራተኞች ቢሯቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ካደረገ በኋላ እሳቸውንም ከአሁን በኋላ የአገሪቷ ወኪል አለመሆናቸውን ገልጾላቸዋል።
አምባሳደሩ ለሮይተርስ የዜና ወኪል " ከግቢው አስወጥተው ቆልፈውብኛል" ብለዋል።
የምያንማር ወታደራዊ ኃይል በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዘው በፈረንጆቹ የካቲት 1/2021 የነበረ ሲሆን ይህም ለሳምንታት የዘለቀ ተቃውሞና አመጽ አስከትሏል።
አምባሳደር ኪያው ዝዋር ሚን ከሥልጣናቸው በኃይል የተነሱት የኖቤል ተሸላሚዋ ኦንግ ሳን ሱ ቺ እንዲመለሱ ጠይቀው ነበር።
በምርጫ ወደ ስልጣን የመጡት ንግ ሳን ሱ ቺ እንዲሁም ፓርቲያቸው ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ ወደ ኃላፊነታቸው እንዲመለሱ የሚጠይቁ በአገሪቱ ውስጥ በተደረጉ ሰልፈኞች ላይ ወታደራዊ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ ሕጻናትን ጨምሮ ከ500 ሰዎች በላይ ተገድለዋል።
አምባሳደር ኪያው ዝዋር ሚን ከኤምባሲው መባረራቸውን በተመለከተ "መሃል ለንደን ላይ የተፈፀመ መፈንቅለ መንግሥት ነው የሚመስለው" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"እንዲህ አይነት መፈንቅለ ስልጣን መካሄድ የለበትም" ሲሉም አክለዋል።
አምባሳደሩ ለንደን ከሚገኘው የምያንማር ኤምባሲ ፊት ለፊት ቆመው የከተማውን ፖሊስ አባላት ሲያነጋግሩ የሚያሳይ ምስላቸው ወጥቷል።
ፖሊስ የኤምባሲው ሠራተኞች ተመልሰው ወደ ቢሯቸው እንዳይገቡ ሲያስጠነቅቅ ነበር።
ከዚህ በኋላ የተቃውሞ ሰልፈኞች በኤምባሲው አካባቢ መሰብሰብ ጀምረዋል።
በመጋቢት ወር አምባሳደር ኪያው ዝዋር ሚኒ፣ አንግ ሳን ሱ ቺ ከእስር እንዲለቀቁ የጠየቁ ሲሆን ለቢቢሲ ሚያንማር "ተከፋፍላለች፤ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት የመግባት አደጋ ተጋርጦባታል" ብለው ነበር።
አምባሳደሩ አክለውም ይህ አስተያየታቸው "አገራቸውን መክዳት" ሳይሆን "በመካከለኛ ስፍራ" መቆማቸውን እንደሚያሳይ ገልፀዋል።
አምባሳደሩ ከዚህ በፊት ኮሎኔል የነበሩ ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶምኒክ ራብ "ጠንካራ እና አገራቸውን ወዳድ" በሚል ተንቆለጳጵሰዋል።
በአሁኑ ጊዜ ምክትል አምባሳደር የነበሩት ቺት ዊን በለንደን የሚገኘውን የኤምባሲውን ኃላፊነት ተረክበው እየሰሩ መሆኑን ሮይተርስ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የዩናይትድ ኪንግደም ውጭ ጉዳይ ቢሮ ለቢቢሲ እንደገለፀው "አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊ ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ" በለንደን የሚገኙት የምያንማር አምባሳደርን በተመለከተ ማብራሪያ መጠየቁን ገልጿል።
የምያንማር ወታደራዊ ኃይል የአገሪቱን መንግሥት በኃይል ካስወገደ በኋላ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።
ይህንንም ተከትሎ በርካታ ምያንማራውያን አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ባለፈው ሳምንት ሱ ቺ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበረ ሕግን በመጣስ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
በዚህ ክስ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 14 ዓመት በሚደርስ እስር ሊቀጡ ይችላሉ።