ሳዑዲ አረቢያ የየመን ግጭትን ለማስቆም ይረዳል ያለችውን የሠላም እቅድ ይፋ አደረገች

በሁቲዎች ቁጥጥር ሥር በምትገኘው የየመን ዋና ከተማ አሁንም ሳዑዱ አየር ጥቃት ይፈጸማል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ለስድስት ዓመታት ገደማ የዘለቀውን የየመን ጦርነት ለማስቆም ሳውዲ አረቢያ አዲስ የሰላም እቅድ አቀረበች፡፡

በሳዑዲ በሚደገፈው መንግስት እና በኢራን በሚደገፉት የሁቲ አማፅያን መካከል በተባበሩት መንግሥታት ቁጥጥር የሚደረግበት የተኩስ አቁም ሃሳብ አቅርባለች።

በዕቅዱ መሠረት ወሳኝ የተባሉ የአየር እና የባህር መግቢያዎችን በድጋሚ መክፈት እና የፖለቲካ ድርድር መጀመርን ያጠቃልላል።

የሁቲ አማጽያን እቅዱ የተጣለውን የአየር እና የባህር እገዳ ለማንሳት የሚበቃ አይመስልም ብለዋል፡፡

ሃሳቡ በሳዑዲ ዋና ከተማ ሪያድ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ልዑል ፈይሰል ቢን ፈርሃን ይፋ ተደርጓል። በርካታ የየመን አካባቢዎችን የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ሃሳቡን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሁቲዎች የተኩስ አቁሙን እንደተቀበሉት ተግባራዊ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው የየመን መንግሥት የቀረበውን እቅድ በደስታ ተቀብሏል። ሁቲዎች ግን እቅዱ “አዲስ ነገር የለውም” ያሉ ሲሆን በዋና ከተማዋ ሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ እና በምዕራባዊው የሁዳይዳህ ወደብ ላይ የተጣለው እገዳ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ያቀረቡት ሃሳብ አለመካተቱን አስታውቀዋል።

“ሳዑዲ አረቢያ የወደብ እና የአየር ማረፊያዎች መዘጋት እንደሚቆም እና በጥምር ጦር ቁጥጥር ስር ያሉ 14 መርከቦች እንዲንቀሳቀሱ ትፈቅዳለች ብለን ጠብቀን ነበር” ሲሉ የሁቲ ዋና ተደራዳሪ መሐመድ አብዱልሰላም ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ ሠላም እንዲሰፍን ከሳዑዲ፣ ከአሜሪካ እና ሸምጋይዋ ኦማን ጋር መነጋገሩ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

የሳዑዲ ባለሥልጣናት በዓለም ላይ እጅግ የከፋ የሰብአዊ ቀውስ የፈጠረውን ግጭት ለማስቆም እርምጃቸውን ከተባበሩት መንግስታት እና ከአሜሪካ ጋር እያቀናጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከቀናት በፊት ሁቲዎች አሜሪካ በአሜሪካ አቀፍ ደረጃ የተኩስ አቁም ስምምነትን ውድቅ አደረጉ ፡፡

የሳዑዲ ጥያቄ ይፋ የሆነው በሁቲ አማፅያን በሃገሪቱ ሀይል እና በደህንነት መሰረተ ልማቶች ላይ የድሮን እና ሚሳኤልጥቃቶችን በጨመሩበት ወቅት ነው፡፡

በሁቲ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ሰነዓ ላይ ሳዑዲ-መራሹ ጦር የቦምብ ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ከዚህ ቀደም የየመንን ሰላም ለመመለስ የቀረቡ በርካታ እቅዶችና ድርድሮች አለመሰካታቸው ይታወሳል።

የየመን ተፋላሚዎቹ በተኩስ አቁሙ ከተስማሙ በተባበሩት መንግሥታት ቁጥጥር የሚደረግበት ሲሆን ለሠላም ድርድር በር ከፋች ነው ተብሏል፡፡

ግጭቱ የተጀመረው በጎርጎሮሳዊያኑ 2014 መገባደጃ ላይ አማጽያኖች አብዛኛውን የምዕራብ የሀገሪቱን ክፍል በተቆጣጠሩበት እና በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው የአረብ መንግሥታት ጥምረት የፕሬዚዳንት አብድራቡህ መንሱር ሀዲን አገዛዝ ለማስመለስ ወታደራዊ ዘመቻ ተጀመረ፡፡

ሪያድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለውን መንግሥት በመደገፍ በ 2015 ወታደራዊው ጥምረት መርታ ብትገባም አማጽያኑን ከስልጣን ለማባረር አልቻለችም፡፡

ከየመን ህዝብ በግምት ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት፣ 20 ሚሊዮን ሰዎች በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ የተመሰረተ ህይወት ይገፋሉ፡፡ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት ከፍተኛ የምግብ እጥረት አለባቸው፡፡

ከግጭቶች በተጨማሪ የየመን የጤና ሥርዓት በመውደቁ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መቋቋም እንዳትችል አድርጓታል፡፡