አሜሪካ ኮሎራዶ ውስጥ አንድ ታጣቂ በከፈተው ተኩስ 10 ሰዎች ገደሉ

የፎቶው ባለመብት, CHET STRANGE
በኮሎራዶ አንድ ግለሰብ ፖሊስን ጨምሮ አስር ሰዎችን በገበያ ሥፍራ ተኩሶ መግደሉን ፖሊስ አስታወቀ።
ጥቃት ፈጻሚው ቆስሎ መያዙም ተሰምቷል።
በገበያ ሥፍራው የደረሰው ጥቃት በዩቲዩብ ቀጥታ መተላለፉም ታውቋል።
ጥቃቱ የደረሰው በአገሪቱ አቆጣጠር ቀን 8፡30 ላይ ሲሆን ግለሰቡ ወደ ገበያ አዳራሹ እንደገባ መተኮስ ጀምሯል።
ጥቃቱ የደረሰበት አካባቢ፣ ቦውልደር ፖሊስ ከ20 ደቂቃ በኋላ በትዊተር ገፁ ላይ "በኪንግ ሱፐርስ የገበያ ስፍራ ተኩስ የከፈተ ግለሰብ አለ" ሲል ጽፎ ነበር።
ከሁለት ሰዓት በኋላ ፖሊስ ሰዎች ከአካባቢው እንዲርቁ አስጠንቅቋል።
አክሎም "ምንም ዓይነት ቴክኒካዊ መረጃ ካያችሁ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አታሰራጩ" ሲል ትዊትር ሰሌዳው ላይ ነዋሪዎቹን ጠይቋል።
ነገር ግን አንዳንድ በአካባቢው የነበሩ ግለሰቦች በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ምስል በማኅበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ ሲያጋሩ ነበር።
በዩቲዩብ የተላለፈው ቪዲዮ ላይ "ምን እንደተከሰተ አላውቅም. . . የተኩስ ድምጽ ሰማሁ። የሆነ ሰው ተመትቶ ወደቀ" የካሜራ ባለሙያው "የሚተኩስ ሰው አለ ዞር በል" ብሎ ሲጮህ ይሰማል።
ከዚያ በኋላም እርሱ ሲሮጥ ከገበያ አዳራሹ ውስጥ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር።
በቪዲዮው ላይ ፖሊስ ደርሶ የገበያ አዳራሹን ሲከብ ይታያል።
በትዊተር ላይ የኮሎራዶ አገረ ገዢ ዣሬድ ፖሊስ "በዚህ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው እና ወዳጆቻቸውን ላጡ መጽናናትንና ብርታትን እመኛለሁ" ብለዋል።
ዋይት ሐውስ በበኩሉ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስለ ጥቃቱ መረጃው እንዲደርሳቸው መደረጉን ገልጿል።












