ያለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና መሰጠት ተጀመረ

የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከዛሬ ሰኞ የካቲት 29/2013 ዓ.ም ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ መሰጠት ተጀመረ።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደዚህ ዓመት የተሸጋገረው የ2012 ዓ.ም ፈተና ከካቲት 29 ጀምሮ እስከ መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በመላው አገሪቱ ይሰጣል።
ከሌሎች ክልሎች በተለየ በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈታኝ ተማሪዎች በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንደሚወስዱ ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም።
ተፈታኞቹ ፈተናቸውን የሚወስዱባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም መቀሌ፣ አክሱም፣ አዲግራት እና ራያ የኒቨርስቲዎች መሆናቸው የትምህርት ሚኒስቴር ቀደም ብሎ አስታውቋል።
ትምህርት ሚኒስቴር በኦንላይን ሊሰጥ የነበረውን የ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በወረቀት እንደሚሆን ቀደም ብሎ መግለጹ አይዘነጋም።
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) 450 ሺህ ታብሌቶች እስከ ታኅሳስ መጨረሻ ድረስ ከውጭ እንደሚገቡ እና 12 ሺህ ላፕቶፖች ደግሞ ለፈታኞች ለማከፋፈል ዝግጁ መሆናችውን ተናግረው ነበር።
በኋላ ላይ ግን በኦንላይን ለመስጠት የታሰበው የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና በኮቪድ-19 ምክንያት መፈተኛ ታብሌቶች በጊዜ ወደ አገር ውስጥ መግባት ባለመቻላቸው ፈተናውን በወረቀት ለመስጠት መወሰኑ ተገልጿል።
የትምህርት ሚኒስቴር በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ለመስጠት እቅድ ይዞ ነበር።
ዛሬ በተጀመረው አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከ250 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሊያበቋቸው የሚችሉ በተለያዩ የትምህርት አይነቶች የሚሰጡ ፈተናዎችን ይወስዳሉ።














