ዓለምን እየከተበ ያለው የዓለማችን ግዙፉ ክትባት አምራች ኩባንያ

የክትባት ብልቃጦች
ታትሟል

የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ዓለምን ለመከተብ እየተሯሯጡ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ከሁሉም ነጥሮ መውጣት የቻለው ሕንዳዊው ኩባንያ ነው።

ሴረም ኢንስቲትዩት ኦፍ ኢንዲያ የተሰኘው ተቋም በዓለማችን ትልቁ ክትባት አምራች ኩባንያ ነው።

በምዕራባዊ ሕንድ በምትገኘው የፑን ከተማ ማምረቻ ፋብሪካውን የገነባው ይህ ኩባንያ በዓመት 1.5 ቢሊዮን ክትባቶችን ያመርታል።

እንደ አስትራዜኔካ ያሉ ክትባቶችን ፈቃድ ወስዶ በገፍ በማምረት ላይም ይገኛል።

"ለአብዛኛዎቹ ክትባቶቹ ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት አደጋውን እያየን ነው ለማምረት ፈቃደኛ የሆንነው" ይላል የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አዳር ፑናዋላ።

"ነገር ግን በጭፍን የገባንበት አይደለም። ምክንያቱ የኦክስፎርድ ሳይንቲስቶችን ከወባ በሽታ ክትባት ጀምሮ እናውቃቸው ነበር።"

ተቋሙ የግል ነው። ዋና ሥራ አስፈጻሚው ፑናዋላ ከሳይንቲስቶች ጋር በመካከር ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ አላዳገተውም።

ነገር ግን ገንዘብ ማሰባሰብ ቀላል አልነበረም። ኩባንያው ከኪሱ 260 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል።

የተቀረውን ገንዘብ የሰበሰበው እንደ ቢል ጌትስ ካሉ ባለሃብቶችና ቀብድ ለመክፈል ከተዘጋጁ ሃገራት ነው።

ሴረም በፈረንጆቹ ግንቦት 2020 ለተለያዩ የኮቪድ ክትባቶች ማምረቻ የሚሆን 800 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ችሎ ነበር።

የሴረም ኢንስቲትዩት ኦፍ ኢንዲያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አዳር ፑናዋላ
የምስሉ መግለጫ, የሴረም ኢንስቲትዩት ኦፍ ኢንዲያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አዳር ፑናዋላ

ሴረም ክትባት በገፍ በማምረት እንዴት ቻለ?

በፈረንጆቹ መጋቢት 2020 ፑናዋላ ቁጭ ብለው ክትባት ለማምረት ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልጋቸው ማስላት ያዙ።

"መስከረም ወር ላይ 600 ብልቃጥ ፈሳሾች አግኝቼ አንድ መጋዘን ውስጥ አስቀምጥኳቸው" ይላሉ ፑናዋላ።

"ጥር ወር ላይ ከ70-80 ሚሊዮን ክትባት ማምረት የቻልነው ነሃሴ ወር ላይ አደጋውን እያየን ክትባት የማምረት ሂደት በመጀመራችን ነው" ሲሉ ባለሃብቱ የስኬታቸውን ምስጢር ይናገራሉ።

"ሌሎችም ክትባት አምራች ኩባንያዎች ይህንን ቢያደርጉ ኖሮ ይሄኔ በርካታ ክትባቶች እጃችን ላይ ይኖሩ ነበር ስል እመኛለሁ።"

ሕንዳዊው የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዓለም አቀፍ መድኃኒት ተቆጣጣሪ ድርጅቶች ክትባት በፍጥነት እንዳይመረት አስተዋፅዖ አድርገዋል ሲሉ ይተቻሉ።

እንደ ዩናይት ኪንግደም፣ የአውሮፓ ሕብረትና የአሜሪካ ምግብና መድኃኒ ቁጥጥር ባለሥልጣን ያሉ ትላልቅ ፈቃድ ሰጪዎች በጋራ ቢሠሩ ኖሮ አሁን ካለን በላይ ክትባት ይኖረን ነበር ይላሉ።

አልፎም ከሕንድ እስከ አውሮፓ ድረስ ያሉ የሃገራት መድኃኒት ቁጥጥር መሥሪያ ቤቶች ዓለም አቀፍ የሆነ ሕግ ቢያወጡ ኖሮ አንድ እርምጃ ወደፊት ተራምደን ነበር ባይ ናቸው።

ፑናዋላ አዲሱን የኮቪድ ዝርያ በተመለከተ ያለውን ፍራቻ ያጣጥላሉ።

"የአስትራዜኔካን ክትባት የወሰዱ ሰዎች እስካሁን በኮቪድ ምክንያት ወደ ሆስፒታል አልሄዱም ወይም አስጊ ደረጃ ላይ አልደረሱም።"

ድርጅቱ ሕንድ ውስጥ እስከሚቀጥለው ነሃሴ ድረስ 300 ሚሊዮን ሰዎች ለመከተብ ዕቅድ ይዟል።

ነገር ግን ብሉምበርግ እንደሚለው እስካሁን ድረስ 56 በመቶ ሰዎች ብቻ ናቸው ክትባት ለመወሰድ ወደፊት የመጡት።

ፑናዋላ ሙያተኛ ያልሆኑ ሰዎች አሊያም ታዋቂ ሰዎች ክትባትን አስመልክቶ የሚሰጡት አስተያየት ጎጂ እንደሆነ ይናገራሉ።

"እባካችሁ ታዋቂ ሰዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ኃላፊነት ይሰማችሁ፤ ወይም ስለክትባት ትንሽ አንብቡ" ሲሉም ይማፀናሉ።