የመርከብ መሃንዲሱ የባህር ላይ "ቆሻሻን" የሙጥኝ ብሎ ከመስመጥ ዳነ

አሮጌ የአሳ ማጥመጃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ከመርከብ ላይ በድንገት የወደቀው ዋና መሃንዲስ "በባህር ላይ ያለ ቆሻሻን ሙጥኝ" በማለቱ ህይወቱ ሊተርፍ እንደቻለ ልጁ አስታውቋል።

በፖስፊክ ውቅያኖስ ላይ ከመርከብ በድንገት የወደቀው ቪዳም ፔርቬርቲሎቭ በውሃ ውስጥ አስራ አራት ሰዓታትን አሳልፏል ተብሏል።

የ52 አመቱ መሃንዲስ በወቅቱ የህይወት አድን ጃኬት አልለበሰም ነበር የተባለ ሲሆን፤ ድንገትም ከነበረበት በኪሎሜትሮች ርቀት ጥቁር ነጥብ በማየቱ ወደዚያው እየዋኘ አምርቷል።

ያየው ነገር ግን አሳ አጥማጆች የጣሏትን እቃ ሲሆን እሱንም ሙጥኝ በማለት ህይወቱ ድኗል።

"ከእነዚያ ሰዓታት በኋላ ስናገኘው ከነበረበት በ20 አመት ያረጀ መስሎና በጣም ደካክሞ ቢሆንም በህይወት በመኖሩ ደስተኞች ነን" በማለት ልጁ ማራት ለኒውዚላንድ የዜና አገልግሎት ተናግሯል።

ቪዳም ፔርቬርቲሎቭ ዜግነቱ ከሉቴንያ ሲሆን ሲልቨር ሰፖርተን የተባለው መርከብ ዋነኛ መሃንዲስ ነው።

በወቅቱም መርከቡ ከኒውዚላንድ የቱዋራንጋ ወደብ በብሪታንያ ግዛት ስር ወዳለችውና በተገለለችው ፒት ካሪን እቃዎችን እያመላለሰ ነበር ተብሏል።

በመርከቡ የሞተር ክፍል ነዳጅ ቅያሬ ጋር ተያይዞ ሙቀትና መደንዘዝ የተሰማው ግለሰብ፤ ነፋስ ለማግኘትም ነው መርከቡ ጫፍ ላይ ቆሞ የነበረው። ሆኖም ከዚያ በኋላ መውደቁ ተሰምቷል።

ማራት አባቱ ራሱን ስቶ እንደወደቀ የሚጠረጥር ሲሆን፤ አባትየው ግን እንዴት እንደወደቀ እንደማያስታውስና ራሱን ውሃ ውስጥ ማግኘቱን መናገሩን አስረድቷል።

ዋና መሃንዲሱ ከመርከብ እንደወደቀ ያልተረዱት መርከበኞችም ትተውት መሄዳቸው ተሰምቷል።

ራሱን ውሃ ውስጥ ያገኘው መሃንዲስ በውቅያኖሱ ውስጥ እየዋኘ ለሰዓታት የቆየ ሲሆን ድንገትም የተጣለ እቃ ከርቀት በማየቱ ወደዚያው አቅንቷል።

ይህንንም እቃ ሙጥኝ ብሎ በመያዝ ህይወቱን ማትረፍ ችሏል።

የመርከቧ ሰራተኞች መሃንዲሱ መጥፋቱን ያወቁት ከስድስት ሰዓታት በኋላ ሲሆን የመርከቧ ካፕቴይንም መርከቧን በማዞር ግለሰቡን ፍለጋ ጀመሩ።

ቪዳም ፔርቬርቲሎቭ መርከቧን በርቀት ሲያያት እጁን በማውለብለብ ለመጣራት ምክሯል። እድለኛም ሆኖ አንደኛው መንገደኛ" ደከም ያለ የሰው ድምፅ ሰምቻለሁ" ማለቱን ተከትሎ እጁን የሚያውለበልበውን መሃንዲስ ሊያዩት ችለዋል።

"በህይወት ለመቆየት የነበረው ፅናትና አልበገር ባይነት የሚገርም ነው ። እኔ ብሆን እስካሁን ሰጥሜ ሞቼ ነበር። እሱ አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያዘወትርና ጤንነቱንም ይጠብቅ ስለነበር ነው መትረፍ የቻለው" ብሏል ልጁ ማራት።