አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጠው የጆንሰን ክትባት ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ተባለ

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጠውን የጆንሰን እና ጆንሰን የኮሮናቫይረስ ክትባት ላይ በሰጠው ግምገማ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ ሆኖ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

ይህም በአሜሪካ ፈቃድ የሚሰጠው ሦስተኛው የኮቪድ -19 ክትባት ለመሆን መንገዱን ከፍቶለታል፡፡

በቀናት ውስጥ ፈቃድ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።

ክትባቱ ከፋይዘር እና ከሞዴርና ክትባቶች አንጻር ወጭ ቆጣቢ አማራጭ ሲሆን በመደበኛው ማቀዝቀዣ መቀመጥ መቻሉም ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

ጆንሰን እና ጆንሰን ከሙከራዎች የተገኙ ውጤቶች ባለፈው ወር ይፋ አድርጓል።

የቤልጂየሙ ኩባንያ ጆንሰን ባወጣው መረጃው መሠረት ክትባቱ ከባድ በሽታ ላይ ውጤታማ መሆኑን አሳይቷል ብሏል፡፡

ጋና በኮቫክስ የክትባት መጋራት ተነሳሽነት የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን በመቀበል የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች ፡፡

የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር (ኤፍዲኤ) የጆንሰን እና ጆንሰን ክትባት ምልክት ያላቸውንም ሆነ ከባድ ህመምን ለመቀነስ "የታወቁ ጥቅሞች አሉት" ሲል ይደመድማል፡፡

በአሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በብራዚል በተካሄዱ የክትባት ሙከራዎች ውጤታማነቱ "በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍተኛ" ሆኖ ተገኝቷል።

ነገር ግን በደቡብ አፍሪካ እና በብራዚል በተስፋፋው አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ዓይነት ላይ ያለው ውጤታማነት አነስተኛ ነበር፡፡

ከከባድ በሽታ ለመከላከል ከ 85 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆኑን መረጃዎች ያሳዩ ሲሆን በአጠቃላይ ውጤታማ የሆነው 66 በመቶ ብቻ ነው፡፡

ክትባቱን ከወሰዱ ተሳታፊዎች መካከል የሞቱ እና ከተከተቡ ከ 28 ቀናት በኋላ ሆስፒታል የገቡም የሉም፡፡

የባለሙያዎች ቡድን ኮሚቴ አርብ ተሰብስቦ ኤፍዲኤ ክትባቱን መፍቀድ አለበት በሚለው ሃሳብ ላይ ይመክራል፡፡

አንድ የኋይት ሃውስ ባለስልጣን ክትባቱ ከኤፍዲኤ የድንገተኛ ጊዜ ፈቃድ ማግኘት ከቻለ አስተዳደሩ በሚቀጥለው ሳምንት ቢያንስ ሶስት ሚሊዮን ክትባት ለማሰራጨት ማቀዱን ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው በሰኔ ወር መጨረሻ ለአሜሪካ የ 100 ሚሊዮን ዶዝ (መጠን) ለማቅረብ በተስማማው መሠረት በመጋቢት መጨረሻ በ 20 ሚሊዮን ዶዝ ለማድረስ አቅዷል፡፡

የትኞቹ ሀገሮች የጆንሰን እና ጆንሰን ክትባትን አዘዙ?

  • እንግሊዝ - 30 ሚሊዮን
  • የአውሮፓ ህብረት - 200 ሚሊዮን
  • ካናዳ - 38 ሚሊዮን
  • የኮቫክስ ሃገሮች - 500 ሚሊዮን