የአፍሪካ የመረጃ ክፍተት፡ የሞቱ ሰዎችን አለመቁጠር የሚያስከትለው ኪሳራ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከ50 የአፍሪካ ሃገራት ስምንቱ ብቻ የተጠናከረ የሞት መመዝገቢያ ሥርዓት እንዳላቸው የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ደርሶበታል።
ይህ ጉዳይ አንድ ሃገር የሰዎችን ሞት ከግምት ውስጥ አለማስገባቷ ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ፖሊሲ ጉዳይንም የሚመለከት ነው።
የአውሮፓ ሃገራት ደግሞ ከአልባኒያ እና ሞናኮ በስተቀር ዓለም አቀፋዊ የሞት ምዝገባ ሥርዓት አላቸው።
በእስያ ደግሞ ከግማሽ በላይ አገራት የሞት መመዝገቢያ መንገድ እንዳላቸው የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
በአፍሪካ ግን ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዚያ፣ አልጄሪያ፣ ኬፕ ቨርድ፣ ሳዎቶሜና ፕሪንሲፔ፣ ሲሼልስ እና ሞሪታኒያ ብቻ ናቸው የሞት መመዝገቢያ መንገድ ያላቸው።
ቢቢሲ ከተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት ኮሚሽን ጋር በጋር በሠራው ጥናት ሁሉም ሃገራት ሞትን የሚመዘግቡበት አንድ መንገድ አላቸው።
ነገር ግን አብዛኛዎቹ መረጃዎች በወረቀት የተቀመጡ እንጂ በአግባቡ የተሰነዱ አይደሉም።
እነዚህ መረጃዎች በወረዳ ደረጃ እንጂ በአገር አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ አይደሉም።
በኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝም ወቅት ሆነ አሁን በኮቪድ-19 ዘመን የሟቾችን ቁጥር በአግባቡ መሰነድ እና የሞት ምክንያትን መመዝገብ ሃብትን ለማከፋፈል ይረዳል።
ስነዳው የእናቶችና ሕፃናት ሞትንም ከግምት ውስጥ ሊያስገባ ይገባል። በርካታ ሕፃናትን ሞታቸው ሳይመዘገብ ይቀራልና።
መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት የምጣኔ ሃብት ኮሚሽን ሠራተኛ የሆኑት ዊሊያም ሙህዋቫ ይህ "ሕፃናቱን ማንነት መንሳት ነው" ይላሉ።
"የሚኖሩ ሰዎችን ለማገዝ፤ የሚሞቱ ሰዎችን መቁጠር አለብን" የሚሉት ደግሞ የተመድ ፖፑሌሽን ፈንድ ባልደረባ ሮሜሽ ሲልቫ ናቸው።
ብዙ ጊዜ ሞታቸው ሳይዘገብ የሚቀረው እጅግ ደሃ የሆኑና በማሕበረሰቡ የተገፉ ናቸው። ሞታቸው አልተመዘገበም ማለት ችግሩን ለመቅረፍ መፍትሔ ማምጫ መላ የለም ማለት ነው በመላት ያክላሉ።
ወደ ኮሮናቫይረስ ስንመጣ ምናልባትም በአንዳንድ ሃገራት የበሽታው ጫና በትክከል አልተዘገበ ይሆናል የሚል ፍራቻ አለ።
በኮቪድ-19 ምክንያት በአፍሪካ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሌላው ዓለም ጋር ሲነፃፀር እጀግ ዝቅ ያለ ነው።
የኮሮናቫይረስ ሞትን መቁጠር
ከመጠን በላይ ሞት ማለት በበሽታው ወቅት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከዚያ በፊት ከነበረው ጊዜ ጋር ማነፃፀር ማለት ነው።
ነገር ግን ይህን ለማጣራት ሞትን በአግባቡ መመዝገብ ይሻል።
ከመጠን በላይ ሞት ተመዘገበ ማለት በኮቪድ-19 ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ጨመረ ማለት ነው።
118 አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሃአራት ላይ በተሠራ ጥናት መሠረት ኮቪድ-19 የጤና ተቋማት ላይ ባስከተለው ጫና ምክንያት ከ1.1 ሚሊየን በላይ ሕፃናትና ከ56 ሺህ በላይ እናቶች ሞተዋል።
ደቡብ አፍሪካና ግብፅ ከስምንቱ አገራት የተሻለ የሞት አመዘጋገብ ስላላቸው ከመጠን ያለፈ ሞትን መለካት ይችላሉ።
እስከ የካቲት ወር ባለው ደቡብ አፍሪካ 138 ሺህ ሰዎች በኮቪድ ምክንያት የተከሰተ ከመጠን ያለፈ ሞት መዝግባለች። ይህ ከመደበኛው ቁጥር ሶስት እጥፍ ከፍ ያለ ነው።
ግብፅም እንዲሁ ከመጠን ያለፈ ሞትን መመዝገብ የቻለች አገር ናት።
ነገር ግን ለበርካታ የአህጉሪቱ አገራት ከመጠን ያለፈ ሞት እየመዘገቡ መሆኑ አለመሆኑን ማጣራት አይችሉም።
በ14 አገራት ከ10 ሞቶች አንዱ ብቻ ነው ከኮቪድ-19 ጋር ግንኙነት ጋር እንዳለው የሚነገረው። ከእነዚህ አገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክና ካሜሩን ይጠቀሳሉ።
ከግማሽ በላይ የሰሃራ በረሃ አገራት ሞትን የሚሰንዱት በወረቀት ነው።
እንደ ኤርትራና ብሩንዲ ያሉ አገራት ደግሞ ሞትን የሚመዘግቡበት ምንም ዓይነት መንገድ የላቸውም።
ኤርትራ እስካሁን ድረስ በኮቪድ-19 ምክንያት ሰባት ሰዎች ብቻ እንደሞቱባት መዝግባለች።
ብሩንዲ ደግሞ ሶስት። ምንም እንኳ የቀድሞው ፕሬዝደንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ባለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ነው የሞቱት የሚል ጥርጣሬ ቢኖርም።
በአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር አንደኛ የሆነችው ናይጄሪያ በፈረንጆቹ 2017 10 በመቶ ሞት ብቻ ነው የመዘገበችው።
ናይጄሪያ ከሚሊየን ሰዎች ዘጠኝ ሞት በኮቪድ-19 ምክንያት ነው ትላለች።
በሌላ በኩል ደቡብ አፍሪካ ከአንድ ሚሊየን ሞት 808 በኮቪድ ምክንያት ነው ስትል ቱኒዚያ ደግሞ 638 መዝግባለች።
እርግጥ ነው በርካታ ሃገራት ይህንን ክፍተት ለመሙላት እየሠሩ ይገኛሉ።
ሴኔጋልና ሩዋንዳ ዓለም አቀፍ የሞት ምዝገባ ሥርዓት ለመከተል ትርፋማ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየሠሩ ነው።
ቶጎ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሲዬር ሊዮን፣ ላይቤሪያና ጋናም እንዲሁ ከአፍሪካ ፊልድ ኤፒዶሞሎጂ ጋር በጥምረት ሞትን ለመሰነድ ደፋ ቀና እያሉ ነው።
አንዳንድ ሃገራት ደግሞ በሞባይል የሞትን መጠን ለመመዝገብና ሰንዶ ለማስቀመጥ ሥር ጀምረዋል።












