ቤኒቶ ሙሶሊኒ ላይ የተኮሰችው አየርላንዳዊት

የፎቶው ባለመብት, Getty Imaes/Italian Ministry of theInterior
ጊዜው በፈረንጆቹ ሚያዝያ 7 1926 ነበር። ቦታው ደግሞ የጣልያኗ መዲና ሮም።
የሃገሬው ሰው በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩ ኃያላን መካከል አንዱ የነበረውን ግለሰብ ለማየት ተኮልኩሏል።
አንዲት አየርላንዳዊት ሴት ግን በሰውዬው ወሬ ብዙም አልተማረከችም። ዓላማዋ ሌላ ነበር።
ድንገት የተኩስ ድምፅ ተሰማ። ሰው ወዲያ ወዲህ ተበታተነ። ለተሰበሰበው ሰው መልዕክቱን ሲያስተላልፍ የነበረው ቤኒቶ ሙሴሊኒም ወደኋላ ተዘረጋ።
ጥይቷ የፈለቀችው ከአየርላንዳዊቷ ሴት አፈሙዝ ነበር። ዒላማዋን አልሳተችም። የሙሶሊኒን አፍንጫ ቦረሸችው።
ሙሶሊኒ ግን አልሞተም። የጣልያኑ መሪ ከተቃጣበት የግድያ ሙከራ መትረፍ ቻለ።
አውሮፓውያን በ20ኛው ክፍለ ዘመን ፋሺስታዊነትን ለመከላከል ከፈፀሟቸው ድርጊቶች መካከል የቫዮሌት ጊብሰን ድርጊት ሁሌም ይነሳል።
ሙሶሊኒን ለመግደል ጥረት ካደረጉ አራት ሰዎች መካከል የተሻለ ሙከራ ያደረገችው እሷ ናት።
አየርላንዳዊቷ ሙሶሊኒን ለመግደል ሙከራ ካደረገች እነሆ መቶ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ዓመታት ይቀሩታል።
ይህን ለማሰብ ደብሊን ውስጥ መታሰቢያ እንዲቆምላት ሥራዎች ተጀምረዋል።
ቫዮሌት ሙሶሊኒ ላይ ሶስት ጥይቶች ተኩሳለች። አራተኛውን ልትለቀው ስትል ግን ሽጉጧ ነከሰ። ይሄኔ የሙሶሊኒ ጠባቂዎች የከበቧት።
የከተማዋ ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ በቁጥጥር ሥር ባያውሏት ኖሮ የጠባቂዎቹ ጡጫ ሲሳይ ትሆን ነበር።
ጣልያን ውስጥ ታሥራ ከቆች በኋላ ወደ እንግሊዝ እንድትሄድ ተደረገ። ይህ የሆነው ጣልያን ውስጥ የፍርድ ሂደቱ ቢካሄድ ውርደት ይሆናል በሚል ነው ይባላል።
ቫዮሌት እንግሊዝ ውስጥ ባለው የቅዱስ አንድሩ የአእምሮ ሕሙማን መታከሚያ ማዕከል ገብታ በስተመጨረሻ በፈረንጆቹ 1956 ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች።
ከእንግሊዛዊ አየርላንዳዊ ከበርቴ ቤተሰብ የተወለደችው ቫዮሌት ክዊን ቪክቶሪያ ውስጥ ነበር የምትኖረው።
አሁን የደብሊን ከተማ በስሟ መታሰቢያ እንዲቆም ረቂቅ አፅድቆ ወደ ሥራ ገብቷል።
የከተማዋ አስተዳደር የሴትዬዋ ድርጊት በታሪክ መዝገብ ብዙም ባለመዘገቡ የሠራችውን 'ፀረ-ፋሺስት' ሥራ የሚዘክር መታሰቢያ ሊቆምላት ይገባል ብሏል።
"የብሪታኒያ መንግሥትና ቤተሰቦቿ የሷን ድርጊት እንደ 'እብድ ሰው' ተግባር ሳይሆን እንደ ፖለቲካ ሊያዩት ይገባል" ይላል ረቂቁ።
በጀግንነቷ ምክንያት የተሰቃየችው
ረቂቁን ለደብሊን ከተማ ምክር ቤት ያቀረቡት ገለልተኛው የከተማው ምክር ቤት አባል ማኒክስ ፍሊን "ቫዮሌት ጊብሰን በአየርላንድና እንግሊዝ መንግሥታት የተረሳች ናት" ሲሉ ይከራከራሉ።
"ልክ እንደበርካታ ሴቶች እጅግ ድፍረት የተሞላበት ድርጊት ብትፈፅምም ተገፍታለች" ሲሉ ለቢቢሲ ሰሜን አየርላንድ ጣቢያ ይናገራሉ።
"ቫዮሌት ጊብሰን የሠራችው ሥራ የሚያሳፍር ነው' 'እብድ ናት' በማለት እንድትደበቅ ተደርጋለች።"
የቫዮሌት ቤተሰቦች ለመታሠቢያ ኃውልቱ ፈቀድ ሰጥተዋል። በሚቀጥሉት ሳምንታትም ረቂቁ ፀድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል።
መታሰቢያ በልጅነቷ ያደገችበት ደብሊን ውስጥ የሚገኘው የሜሪዬን አደባባይ እንዲሆንም ሐሳብ ቀርቧል።
ደብዳቤ ለቸርችል
የቫዮሌት ታሪክ ወደ አደባባይ ብቅ ያለው በፈረንጆቹ 2014 አርቲኢ የተሰኘው ራድዮ ጣቢያ በሠራው ዘጋቢ ቅንብር ምክንያት ነው።
ዘገባው 'ሙሶሊኒ ላይ የተኮሰችው ሴት' ከተሰኘው መፅሐፍ ላይ የተወሰደ ነው።
ታሪኳ ላይ እንደተመዘገበው ቫዮሌት ከቅዱስ አንድሩ ሆስፒታል እንድትለቀቅ በወቅቱ ለነበሩ ኃያላን መሪዎች ደብዳቤ ፅፋ ነበር።
ከእነዚህ መካከል የአሁኗ የእንግሊዝ ንግሥት ኤሊዛቤት ይገኙበታል።
ሌላኛው ደብዳቤ የተላከው በወቅቱ የእንግሊዝ መሪ ለነበሩት ዊንስተን ቸርችል ነበር።
ቸርችል በደብሊን ከተማ ባደጉ ወቅት ከቫዮሌት ጋር እውቅና ሳይኖራቸው አይቀርም ይላል ታሪኳን የሚዘግበው መፅሐፍ።
ለዊንስተን ቸርችል የተፃፈው ደብዳቤ አሁንም አለ። ነገር ግን በወቅቱ ደብዳቤው ለቸርችል ሊደርስ አልቻለም።
የራድዮ ዘገባው አዘጋጆች ወደ ጣልያን ሄደው በሠሩት ጥናት መሠረት ሙሶሊኒ ላይ ከተሞከሩ ግድያዎች መካከል ብዙ መረጃ የተሰበሰበው በቫዮሌት ዙሪያ ነው።
"ይህን ድርጊት የፈፀመው ወንድ ቢሆን ኖሮ ይሄን ሃውልት ወይም ሌላ መታሰቢያ ተሠርቶለት ነበር። እሷ ሴት ስለነበረች ታሠረች። እኛ ታሪኩን ለሕዝብ ይፋ በማድረጋችን ደስተኞች ነን" ይላሉ የዘገባው አዘጋጆች።
ቤኒቶ ሙሶሊኒ ማነው?
የሙሶሊኒ ብሔራዊ ፋሺስት ፓርቲ ጣልያን ውስጥ ወደ ሥልጣን የመጣው ከአንደኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ነው።
'ብላክሸርትስ' በተሰኙ ታጣቂዎች የሚደገፈው ፖርቲ ተቀናቃኞችን በኃይል ያስፈራራ ነበር።
ፋሺስቱ ፓርቲ በ1920ዎቹ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ዴሞክራሲያዊ የሚባሉ ተቋማትን አፈራረሰ።
ሙሶሊኒ የጣልያን አምባገነናዊ መሪ ሆነው የተሾሙት በፈረንጆቹ 1925 ነበር።
ሙሶሊኒ በስፔን የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የጁኔራል ፍራንቺስኮ ፍራንኮ ደጋፊ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ደግሞ የአዶልፍ ሂትለር ቀኝ እጅ ነበር።
ሙሶሊኒ የሂትለርን አንዳንድ ፖሊሲዎች ወስዶ በ1938 የጣልያኑ አይሁዳዊያን ሙሉ በሙሉ መብታቸው እንዲገፈፍ አድርጎ ነበር።
በአይሁዶች ጅምላ ጭፍጨፋ [ሆሎኮስት] ወቅት ከ7 ሺህ 500 በላይ የጣልያን አይሁዶች እንደተገደሉ ይታመናል።
ኢትዮጵያ በጣልያን ለሁለተኛ ጊዜ የተወረረችው በሙሶሊኒ አምባገነናዊ ሥርዓት ወቅት ነበር።
ሙሶሊኒ ከምዕራባዊያን ጦር ለማምለጥ ሲሞክር በጣሊያን ነፃ አውጭዎች ተይዞ የተገደለው በፈረንጆቹ 1945 ነው።












