ጥቁሩ የማክዶናልድስ ባለቤት ኩባንያው ዘረኛ ነው ሲል ከሰሰ

ኸርብ ዋሺንግተን

የፎቶው ባለመብት, Handout

ታትሟል

የቀድሞ ፕሮፌሽናል ቤዝቦል ተጫዋች የነበረው ግለሰብ ማክዶናልድስ የተሰኘው ፈጣንና ትኩስ ምግብ አቅራቢ ድርጅት ዘረኛ ነው ሲል ከሷል።

ሰውዬው በአንድ ወቅት በአሜሪካ በጥቁሮች ዘንድ ትልቁ የማክዶናልድስ ሱቆች ባለቤት ነበር።

ኸርብ ዋሺንግተን እንደሚለው ማክዶናልድስ ለነጮች የሚሰጠውን ያክል ቦታ ለጥቁር ባለቤቶች አይሰጥም።

እንደ ሰውዬው ከሆነ ጥቁር የማክዶናልድስ ባለቤቶች በአብዛኛው ጥቁሮች ወደሚኖሩበት የተጨናነቀ ሥፍራ ሄደው ቅርንጫፍ እንዲከፍቱ ነው የሚደረገው።

ዋሺንግተን እንደሚለው እሱ እኒህን ቅራኔዎች በማንሳቱ ምክንያቱ ድርጅቱ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ በቀል መርጧል።

ማክዶናልድስ ግን ችግሩ የኛ ሳይሆን የባለቤቱ 'አስተዳደር' ጉዳይ ነው ብሏል።

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ የተነሳበትን ክስ እየመረመረ መሆኑን ገልፆ ነገር ግን "ዋሺንግተን እኛ ለደንበኞቻችን የማንመኘው የቢዝነስ ፈተና ገጥሞት ነበር" ብሏል።

"ይህ የመነጨው ለዓመታት ከነበረ የአስተዳደር ችግር ነው። የሱ ድርጅት የኛን ቅደመ ሁኔታዎች ማሟላት አልቻለች" ይላል መግለጫው።

አክሎም "የሱ ቅርንጫፎች የጤናና ንፅህና እንከኖችን ጨምሮ የተለያዩ ቅሬታዎች ይነሱበታል" ሲል ዋሺንግተንን ይወቅሳል።

ማክዶናልድ ከጥቁር የቅርንጫፍ ባለቤቶች መሰል ክስ ሲቀርብበት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ባለፈው ዓመት 50 ያክል የቀድሞ የቅርንጫ ባለቤቶች ኩባንያው ብዙም ደንበኛ ወደ ሌለባቸው ቦታዎች ሄደን ቅርንጫፍ እንድንከፍት አድርጎናል ሲሉ ከሰውት ነበር።

ፕሮፌሽናል ቤዝቦል ተጫዋች የነበረው ዋሺንግተን የመጀመሪያውን የማክዶናልድስ ቅርንጫፍ የከፈተው በ29 ዓመቱ በፈረንጆቹ 1980 ነበር።

ነገር ግን ኩባንያው በተደጋጋሚ ቅርንጫፎቹ እንዳያድጉ ያግደው እንደነበር ይናገራል።

ከእነዚህ መካከል ከነጭ ባለቤቶች ቅርንጫፍ እንዳይገዛ መከልከል፣ ለነጮች የሚደረው የገንዘብ እርዳታ ለእሱ እንዳይደርስ ማገድ ይገኙበታል።

ነገር ግን እነዚህን ፈተናዎች ተቋቁሞ በአንድ ወቅት 27 ቅርንጫፎች በማንቀሳቀስ በአሜሪካ ትልቁ ጥቁር የማክዶናልድስ ባለቤት መሆን ችሎ ነበር።

በአሁኑ ወቅት 14 የማክዶናልድስ ቅርንጫፎች እያንቀሳቀሰ ይገኛል።

ዋሺንግተን ኩባንያው ላይ ክስ መመሥረቱን ባሳወቀ ሰዓት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ "ኩባንያው አንድ ቀን ልክ ቃል በገባው መሠረት ሁሉንም ደንበኛ እኩል ያስተናግዳል የሚል ተስፋ ነበረኝ" ብሏል።

እሱ እንደሚለው በርካታ ቅሬታዎች በማሰማቱ ምክንያት ከ2017 [በፈረንጆቹ] ጀምሮ ኩባንያው እሱን ለማጥፋት የበቀል እርምጃ ሲወስድ ነበር።

የሌሎች ቅርንጫፎቹን ውል ለማራዘም ከፈለገ አንዳንድ ቅርንጫፎቹ እንዲሸጥ ያስገድዱት እንደነበር ይናገራል።

ማክዶናልድስ የተሰኘው ፈጣን፣ትኩስ ምግብ አቅራቢ ኩባንያ ቅርንጫፎቹን ለተለያዩ ባለቤቶች በመሸጥ ነው የሚንቀሳቀሰው።

በአሜሪካ ጥቁር የማክዶናልድስ ቅርንጫፍ ባለቤቶች በ1998 377 ነበሩ። አሁን ግን ቁጥራቸው ወደ 186 ወርዷል።

ድርጅቱ የጥቁር ባለቤቶች ዓመታዊ ገቢ ከነጮች ጋር ሲነፃፀር በ700 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያነሰ ነው ይላል።

ነገር ግን ባለፈው ሐምሌ የስብጥር ማነቃቂያ እርምጃ ወሰድኩ ያለው ኩብንያው በጥቁሮች የተያዙ ቅርንጫፎች ሽያጭ እየጨመረ ነው ሲል ተደምጧል።