እግር ኳስ፡ ቀጣይ መድረሻው ያልታወቀው የሊዮኔል ሜሲ ጉዳይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የባርሴሎና እና የአርጀንቲናው የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ክለቡ ባርሴሎናን ሊለቅ እንደሚችልና ሌላ አገር ሄዶ መጫወት እንደሚፈልግ በተናገረ ጊዜ በርካቶች ዜናውን በእንባ ነበር የተቀበሉት። ቤሰቦቹን ጨምሮ።
ነገር ግን መጨረሻ ላይ ሜሲ ያሰበው ነገር ሳይሆን ቀረና በዘንድሮው የላሊጋ የውድድር ዓመት በባርሴሎና ለመቆየት ተገዷል።
ሜሲ ከባርሴሎና ጋር የገባው ውል የሚያበቃው በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት 2021 ነው። ከዚያ በፊት ተጫዋቹን መግዛት የፈለገ ክለብ ደግሞ 700 ሚሊዮን ዩሮ ማውጣት ይኖርበታል።
ሜሲ ግን ከባርሴሎና ጋር በተፈራረመው ውል ላይ "'ከፈለኩ በነፃ እንድሰናበት' የሚል አንቀፅ አለ፤ እሱን ተግባራዊ ማድረግ እፈልጋለሁ" ብሎ ነበር።
ሊዮኔል ሜሲ ባርሴሎናን የተቀላቀለው የ12 ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር። 10 የላ ሊጋ ዋንጫ ጨምሮ 34 ዋንጫዎችን ከቡድን አጋሮቹ ጋር ማንሳት ችሏል። ከዓመታት በኋላ ግን የ33 ዓመቱ ሜሲ ጫማውን የሚሰቅለው በየትኛው ክለብ ነው የሚለውን መወሰን ይጠበቅበታል።
ምንም እንኳን ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች ባርሴሎናን ለመልቀቅ ፍላጎት አሳይቶ የነበረ ቢሆንም እንደአሁኑ ግን ክለቡን ለመቀልቀቅ የተቃረበበት አጋጣሚ አልነበረም።
የዚያን ጊዜ ወደ አርጀንቲና መመልስን ችላ በማለት ስፔን ውስጥ ከአባቱ ጋር ለመሆን መወሰኑ በርካታ የቤተሰቡ አባላትን ልብ ሰብሮ ነበር። ውሳኔው ህይወቱን የመቀየር ኃይል ነበረው።
መጨረሻው ያልታወቀውን የሜሲ ጉዳይ በድጋሚ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገው ደግሞ ባርሴሎና በዚህ ሳምንት በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ከፈረንሳዩ ፒኤስጂ ጋር ያለበት ጨዋታ ነው። ፒኤስጂዎች ከጅምሩ የሊዮኔል ሜሲ አድናቂ መሆናቸውንና ክለቡን እንዲቀላቀል እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ጨዋታው በተቃረበ ቁጥር ደግሞ የፈረንሳይ መገናኛ ብዙሃን ስለ ሜሲ የተለያዩ መረጃዎችን ይዘው መውጣት ጀምረዋል። አንድ ጋዜጣ ደግሞ ሊዮኔል ሜሲ የፒኤስጂን ማልያ ለብሶ የሚያሳይ ዘገባ ይዞ ወጥቷል። ተጫዋቹ ፒኤስጂን ሊቀላቀል የሚችልባቸው ሁኔታዎችንም በዝርዝር አስነብቧል።
የፒኤስጂው ኮከብና የቀድሞ የባርሴሎና ተጫዋች ኔይማርም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሰጥቷል። ባለፈው የፈረንጆቹ ታኅሣስ ላይ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድን ካሸነፉ በኋላ ኔይማር "ከዚህ በኋላ ከምንም በላይ የምፈልገው ከሜሲ ጋር በድጋሚ መጫወት ነው፤ ከእሱ ጋር በሜዳ ላይ ሆኜ እግር ኳስን ማጣጣም እፈልጋለሁ" ብሎ ነበር።
"ከፈለገ እኔ በምጫወትበት ቦታ ሊጫወት ይችላል፤ ምንም ችግር አይኖረውም። እርግጠኛ ነኝ። እሱ ብቻ ፒኤስጂን ይቀላቀል እንጂ ሌላው አሳሳቢ አይደለም። ከእሱ ጋር በድጋሚ መጫወት ትልቁ ህልሜ ነው። በሚቀጥለው የውድድር ዓመት ይህ እንደሚሆን ደግሞ እርግጠኛ ነኝ" ሲል አስተያቱን ሰጥቶም ነበር።
ሌሎቹ የፒኤስጂ ተጫዋቾች ዲ ማሪያ እና ቬራቲ እንዲሁም የፒኤስጂ ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ሊአንድሮ ፓሬዴዝ ሊዮኔል ሜሲ ባርሴሎና መጫወት ካልፈለገ ቡድናቸውን እንዲቀላቀል እንደሚፈልጉ በግልጽ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሜሲ ከዚህ ሁሉ ድራማ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን ባስተላለፈው መልዕክት ሰዎች በእሱ ጉዳይ ላይ እየሰጡ ባለው አስተያየት ደስተኛ እንዳልሆነና የቅርብ ወዳጆች የሚላቸው ጭምር ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ጫና በማሳደራቸው መገረሙን ገልጾ ነበር።
ነገሮችን ይበልጥ ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ ኔይማር ወደ ባርሴሎና የመመለስ ሀሳቡን በመተው በፒኤስጂ ለመቆየት መወሰኑና ኪሊያን ምባፔም የመሄድ ሐሳቡን በመተው ከክለቡ ጋር ድርድር መጀመሩ ነው። እነዚህ የእግር ኳስ ክዋክብት በፒኤስጂ የሚቆዩ ከሆነ ሜሲም ሊቀላቀላቸው እንደሚችል ይገመታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሜሲ ባርሴሎናን እንደሚለቅ ባስታወቀ ጊዜ መዳረሻው በቀድሞው የባርሴሎና አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ሊሆን እንደሚችል በስፋት ሲገለጽ ነበር። እንደውም በሐሳብ ደረጃ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሎም ነበር።
የአሁኑ የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ከ2008 እ.አ.አ ጀምሮ እስከ 2012 ድረስ ለአራት ዓመታት ያህል ሜሲን አሰልጥኖታል። በአራት ዓመት ጊዜውም ሦስት የላሊጋና ሁለት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አንስቷል።
በአንድ ወቅትም "እኔ በጣም እድለኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ቢያንስ የዓለማችንን ምርጡን ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲን አሰልጥኜዋለሁ" በማለት ጋርዲዮላ ለሜሲ ያለውን አድናቆት ገልጿል።
ይህ ወደጅነታቸውም አሁን እንደገና ሊያገናኛቸው ይችላል የሚለውን ግምት በበርካቶች ዘንድ አሳድሯል። ነገር ግን ጋርዲዮላ የማይታሰብ ነው ብሏል። "እዚያው [ባርሴሎና] ይቆያል፤ የእኔ ፍላጎትም ይህ ነው" በማለት።
የባርሴሎናው የምንጊዜም ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ስድስት ጊዜ የባሎን ዶር አሸናፊ በመሆን የምድራችን ብቸኛ ተጫዋች ሲሆን በባርሳ ቆይታው 10 የላሊጋና አራት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አሸንፏል። እስከ ፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ በባርሳ የሚያቆየው ኮንትራትም አለው።
የሜሲ ወደ ማንቸስተር ሲቲ የመምጣት ጉዳይ ደግሞ እንደ ኬቨን ደብራይነ ያሉ የክለቡ ኮከብ ተጫዋቾችን ምቾት የነሳ ሆኗል። ምክንያቱም ደብራይነ ከክለቡ ጋር የሚያቆየውን ኮንትራት ለመፈራረም እያመነታ ነው። ክለቡ ለተጫዋቹ ያቀረበው ገንዘብ ደብራይነ ከሚያስበውና ከሚፈልገው በእጅጉ ያነሰ ነው። አንዳንዶ ደግሞ ማንቸስተር ሲቲ ገንዘብ እየቆጠበ ያለው ምናልባት ሜሲ ከመጣ ለእሱ የሚሆን ክፍያ እንዲኖረው ይላሉ።
ወጣም ወረደ ግን በመጪው መጋቢት ወር ባርሴሎና እግር ኳስ ክለብ የሚያደርገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የክለቡን ውሳኔም ሆነ የሊዮኔል ሜሲን መዳረሻ ፍንጭ የሚሰጥ ይሆናል።
ሊዮኔል ሜሲ 644ኛ ጎሉን ለክለቡ ባርሴሎና በማስቆጠር የፔሌን ክብረ ወሰን የሰበረው ታኅሣስ ወር ላይ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሜሲ የከፍተኛውን ግብ ክብረ ወሰን በእጁ ለማስገባት የቻለው ቡድኑ ባርሴሎና ከሪያል ቫላዶሊድ ጋር በነበረው ግጥሚያ ከመረብ ባገናኘው ጎል ነው። በዚህም ሜሲ ለአንድ ክለብ ብዙ ጎሎች በማስቆጠር የብራዚላዊውን እግር ኳሰኛ ፔሌ ክብረ ወሰን ሰብሯል።
የ33 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ባርሴሎና ሪያል ቫላዶሊድን ባሸነፈበት ጨዋታ ከክለብ አጋሩ ፔድሪ የተቀበላትን የቅንጦት ኳስ ወደ ጎል ቀይሮ ነው ክብረ ወሰኑን የጨበጠው።
ብራዚላዊው የእግር ኳስ ጥበበኛ ፔሌ ለሳንቶስ ክለብ ከ1956 እስከ 1974 ተጫውቷል። ለ19 የውድድር ዘመኖች ለአገሩ ክለብ የተጫወተው ፔሌ 643 ጎሎች ከመረብ ማገናኘት ችሏል።
በቀጣይ ምን እንጠብቅ?
ሜሲ በባርሴሎና ቆይታው ከፒኤስጂ ጋር ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ኳስን ከመረብ ማገናኘት ችሏል። በአሁኑ ጊዜ መወሰን የቻለው ብቸኛው ነገር ደግሞ የዘንድሮው የውድድር ዓመት እስከሚጠናቀቅ ድረስ ባርሴሎናን አለመልቀቅ ነው።
በዋነኛነት የሚጠብቀው ነገር ደግሞ መጋቢት ላይ የሚካሄደውን የክለቡ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ነው። እንደሚያሸንፉ በስፋት እየተነገረላቸው የሚገኘው የቀድሞው ፕሬዝደንት ሁዋን ላፖርታ ሲሆኑ እኚሁ ሰው የሚያሸንፉ ከሆነ ሜሲ በባርሴሎና የመቆየቱ ነገር የተረጋገጠ ሊሆን ይችላል እያሉ ነው የቅርብ ሰዎች ነን የሚሉ ተንታኞች።
እኚህ ሰው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ ከዕቅዳቸው ውስጥ አራቱን ፈረንሳያውያን በመሸጥ እስከ 200 ሚሊየን ዩሮ መሰብሰብ የመጀመሪያው ነው። የሚሸጡት ተጫዋቾች አንትዋን ግሪዝማን፣ ኦስማን ዴምቤሌ፣ ክሌመንት ሎንግሌ እና ሳሙኤል ኡምቲቲ ናቸው።
ከእነዚህ ተጫዋቾች ሽያጭ በሚገኘው ገንዘብ ደግሞ እንደ ዴቪድ አላባ፣ ኤሪካ ጋርሺያ እና ኤርሊንግ ሃላንድን የመሳሰሉ ክዋክብትን መሸመት ነው።
አሁን ዋናው ጥያቄ ኮሮናቫይረስ እግር ኳስን ጨምሮ በርካታ እንቅስቃሴዎች ባሽመደመደበት ወቅት ይህን ያክል ገንዘብ (200 ሚሊየን ዩሮ) አውጥቶ ተጫዋቾችን የሚገዛው ማነው? የሚለው ነው።
ሜሲ ወደ አሜሪካ የመሄድ ፍላጎትም እንዳለው አልደበቀም። ባለቤቱ አንቶኔላ ከቀድሞው የክለብ ጓደኛው ሴስክ ፋብሬጋስ ባለቤት ጋር ጥብቅ የሆነ ወዳጅነት መስርታለች። ፋብሬጋስ እና ባለቤቱ ደግሞ ሜሲና ባለቤቱ ወደ አሜሪካ መጥተው የመጨረሻዎቹን የእግር ኳስ ዓመታት እዚያ እንዲያሳልፉ ይፈልጋሉ።
በተደጋጋሚም ወደ አሜሪካ እንዲመጡ ለማሳመን ሲጥሩ ነበር።
ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ ባርሴሎና ሪያል ማድሪድንም ሆነ አትሌቲኮ ማድሪድን እንዲሁም ሲቪያን አሸንፎ አያውቅም። ድል ለሚጠማው ሜሲ ደግሞ ይህ ትልቅ ቁጭት ነው። ባርሴሎና በቶሎ እነዚህን ክለቦች ማሸነፍ እንደሚችል ማሳየት ካልቻለ ሜሲ ምናልባትም እስከወዲያኛው ባርሴሎናን ለቅቆ ሊሄድ ይችላል።















