ለድንገተኛ አገልግሎት የደወሉት ጥንዶች ህፃን በድብደባ ለሞት መዳረጉን አጋለጡ

ጨቅላው ህፃን

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

ፈረንሳያዊ ጥንዶች የሶስት አመት ጨቅላን ደብድበው ለሞት በመዳረጉ የእስር ቅጣት ተበየነባቸው።

የ28 አመቱ ሎይክ ቫንታል የሴት ጓደኛውን ልጅ ደብድቦ ለሞት በመዳረጉ የ20 ዓመት እስራት ተከናንቧል።

ክስተቱ የተፈጠረው በአውሮፓውያኑ 2016 ሲሆን የ19 አመት እድሜ ያላት እናቱ ካሮሊን ሌቶሊ ጨቅላው ራሱን በሳተበት ወቅት ድንገተኛ አገልግሎት ለእርዳታ ደውላ ነበር።

እናም በስልክ አገልግሎት የሚሰጣት ሰው እስኪመጣ ድረስ በስልክ እንድትጠብቅ በተነገራት ወቅት ድምጿ እየተቀዳ እንደሆነ ሳታውቅ ልጁ እንደተደበደበ አጋልጣለች።

"ሲመጡ ከደረጃ ላይ ወድቆ ነው እላለሁ" ስትል የሚሰማ ሲሆን በምላሹ የወንድ ጓደኛዋም " አዎ ደረጃ ያሳምናል አይደል? የአፓርትመንቱ ደረጃ፤ የሚያጋልጡ ነገሮችን በሙሉ ልደብቅ" በማለት ምላሽ ሲሰጣት ተቀድቷል።

የህምና ባለሙያዎች የጥንዶቹ አፓርትመንት ሲደርሱ ህፃኑ ራሱን ስቶና ሰውነቱ በላልዞ አግኝተውታል።

ለህምና ሆስፒታል ቢወስዱትም ህይወቱ ወዲያው አልፏል።

ፖሊስ ሎይክን ባፋጠጠው ወቅት የሴት ጓደኛውን ካሮልን ከተዋወቀበት ጀምሮ ለሶስት ወራት ያህል ህፃኑን በተደጋጋሚ ይመታው እንደነበር አምኗል።

በዚህ ሳምንት አርብ ለሳምንት ያህል በቆየው የፍርድ ሂደት ሆን ብሎ ጥቃትን በመፈፀም ለሞት ዳርጎታል በሚል ክስ ጥፋተኛ ሆኖ ያገኘው።

በፍርድ ሂደቱም ዳኛዋ የህፃኑን እናት ካሮልን ስለ ልጇ መደብደብ ለፖሊስ ለምን እንዳላሳወቀች ጠይቃት ነበር። "በጣም ፈራሁ። እንዲረዱኝ ልደውል ፈልጌ ነበር ነገር ግን አላደረግኩትም" ብላለች።

አካላዊ ጥቃት ሲደርስ ሪፖረት ባለማድረጓ የሶስት አመት እስር ተበይኖባታል።