በኢትዮጵያ የዘይት እጥረትን እንደሚቀርፍ ተስፋ የተጣለበት ፋብሪካ ተመረቀ

የፎቶው ባለመብት, Birhane Garedew
በኢትዮጵያ የዘይት አቅርቦት ላይ ያለውን እጥረት ሊቀርፍ ይችላል የተባለ ግዙፍ ፋብሪካ በዛሬው ዕለት ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ፋብሪካውን መርቀው ከፍተውታል።
ፋብሪካው በአማራ ክልል ቡሬ ከተማ የሚገኝ ሲሆን 4.5 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበትም ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ አካል የሆነው ፌቤላ ኢንደስቱሪያል ኮምፕሌክስ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በቀን 1.5 ሚሊዮን ሊትር የዘይት ምርቶች ለኢትዮጵያ ገበያ የማቅረብ አቅም አለው ተብሏል።
በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የዘይት ምርት ፍላጎት ለማሟላት መንግሥት በውጪ ምንዛሬ፣ የዘይት ምርት ከውጪ ወደ አገር ውስጥ እያስገባ ይገኛል።
የኢንደስትሪያል ኮምፕሌክሱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳምጤ ስማቸው ኮምፕሌክሱ የሚያመርተው የዘይት ምርት 45 በመቶ የአገሪቱን ፍላጎት የሚሸፍን ይሆናል ብለዋል።
ኮምፕሌክሱ ከቅባት እህሎች የሚመረቱ የዘይት ምርቶችን እና የፓልም ዘይትን ለገበያ ያቀርባል።
እንደ አቶ ዳምጤ ገለጸ ከሆነ ከቅባት እህሎች ለሚመረተው ዘይት ግብዓቱን ከአገር ውስጥ ለመሰብሰብ ታቅዷል። በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው በቀን ከ750ሺህ በላይ ሊትር የቅባት እህል ዘይት ለማምረት የሚያስፈልገውን ግብዓት ማቅረብ የሚችል የአገር ውስጥ አቅራቢ አለመኖሩን ይናገራሉ።
በዚህም ምክንያት ፋብሪካው ወደፊት ለቅባት እህል ዘይት ምርቱ የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማግኘት የራሱን እርሻ እያዘጋጀ መሆኑን አቶ ዳምጤ ተናግረዋል።
ለፓልም ዘይት ምርት ግን ድፍድፍ ግብዓቱን ከውጪ በማስገባት በፋብሪካው የማጣራት ሥራ እንደሚሰራ አቶ ዳምጤ አስረድተዋል።
ኮምፕሌክሱ የሚያመርታቸው የዘይት አይነቶች ለገበያ የሚቀርቡበት ዋጋ በቀጣይ ቀናት እንደሚተመን የሚናገሩት አቶ ዳምጤ፤ የተሻለ ጥራት ያለውን ምርት በተወዳዳሪ ዋጋ ለሕብረሰቡ ማቅረብ አላማችን ነው ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Birhane Garedew
በ30 ሄክታር መሬት ላይ የሰፈረው ፋብሪካ፤ ያመረተውን ዘይት ለማሸግ የተለያየ መጠን እና ቅርጽ ያላቸው ፕላስቲኮች እና ካርቶን እንደሚያመርት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
ዛሬ በተመረቀው ኢንደስትሪያል ኮምፕሌክስ ከዘይት ምርቶች በተጨማሪ የሰሊጥ ምርትን በመቁላት እና በመፈተግ እሴት ጨምሮ ወደ ውጪ አገር ይልካል።
ከዚህ በተጨማሪ ኢንደስትሪያል ኮምፕሌክሱ የሳሙና እና የማርገሪን ፋብሪካም አለው።
ፌቤላ የኢንደስቱሪያል ኮምፕሌክስ በቡሬ ከተማ በ4.5 ቢሊዮን ብር የተገነባ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለ1ሺህ ሰዎች የሥራ እድልን ፈጥሯል። ኮምፕሌክሱ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ እስከ 3ሺህ ሰዎችን እንደሚቀጥር አቶ ዳምጤ ለቢቢሲ ተናግረዋል።












