አይ ኤስ በግፍ የጨፈጨፋቸው የያዚዲ ማኅበረሰብ አስክሬኖች ተሰበሰቡ

የሬሳ ሳጥን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በሰሜናዊ ኢራቅ በኢስላሚክ ስቴት ((IS) በአሰቃቂ ሁኔታ የተጨፈጨፉ የያዚዲ ማኅበረሰብ አባላት አስክሬን ወደ ትውልድ ቦታቸው በማምጣት በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል።

ጽንፈኛው የአይኤስ ቡድን አካባቢውን በአውሮፓውያኑ በ2014 በተቆጣጠረ ጊዜ የጅምላ ጭፍጨፋ ያደረሰባቸው በዋናነት በያዚዲ እምነት ተከታዮች ነበር።

ለጊዜው የ104 የያዚዲ ማኅበረሰብ አባላት አስክሬን በጅምላ ከተቀበሩበት ወጥቶ ወደ ትውልድ አገር ሰሜን ኢራቅ ተወስዶ በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል።

አስክሬናቸው በክብር እንዲያርፍ የተደረገው ኮቾ በምትባል ገጠር ከሲንጃር ተራራ አቅራቢያ በኒነቫህ ክልል ውስጥ ነው።

በአይኤስ አመራር ወቅት በሺህ የሚቆጠሩ የያዚዲ ወንዶች በግፍ የተጨፈጨፉ ሲሆን ህጻናት በባሪያነት እንዲያገለግሉ ተደርገዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች ተደፍረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽንፈኛው አይ ኤስ በያዚዲ ማኅበረሰብ የፈጸመው ተግባር የዘር ማጥፋት ሙከራ ነው ሲል አውጆታል።

እነዚህ አሁን አስክሬናቸው ከጅምላ መቃብር የተሰበሰበው የ104 ያዚዲዎች ሁሉም ወንዶች ሲሆኑ አይኤስ በ2014 የቀላቸው ናቸው ተብሏል።

የሬሳ ሳጥን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አስክሬኖቹ ወደ ትውልድ አገራቸው ኮቾ በመወሰዳቸው በፊት በባግዳድ ሐሙስ ዕለት የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ተደርጎላቸዋል።

የያዚዲ ማኅበረሰብ የሰብአዊ መብቶች አራማጅ ሚርዛ ዲናዪ እንዳሉት ይህ አስክሬን ሰብስቦ በክብር የማሳረፍ ሂደት ለተጎጂ ቤተሰቦች የመጀመርያ እርምጃ ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ ግፍ የተፈጸማቸው ሴቶችና ሕጻናት ካሳ እንዲያገኙ ማድረግ ሂደት ይቀጥላል ብለዋል።

ያዚዲ ማኅበረሰብ በሰሜን ኢራቅ የሚኖሩ የያዚዲ እምነት ተከታዮች ስብስብ ሲሆን ቁጥራቸው እስከ ግማሽ ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል።

የያዚዲ ሃይማኖት ጥንታዊ ዞሮስትሪያኒዝምና ጥንታዊ የሜሶፖቶሚያ እምነቶችን የቀላቀለ ነው። በርካታ የእምነቱ ሥርዓቶች ደግሞ የእስልምናና የጥንታዊ ክርስትናና መልኮችም አሉት።

በያዚዲ ሃይማኖት መሠረት አንድ ሰው ያዚዲ ሆኖ ይወለዳል እንጂ ከሌላ ሃይማኖት ወደ ያዚዲነት ሊቀየር አይችልም።

አንድ የያዚዲ እምነት ተከታይ የመጨረሻው ቅጣት ከያዚዲ ማኅበረሰብ መባረር ነው። ይህ ለያዚዲዎች አስፈሪ ቅጣት በመሆኑ እምነታቸውን በየትኛውም የስቃይ ሁኔታ ውስጥ ይዘውት ይቆያሉ እንጂ ወደ ሌላ ሃይማኖት ሽግግር ማድረግ የማይሞከር ተግባር ነው።

ያዚዲዎች መላክ ታውስ ለሚሉት የአምላክ ክፋይ በቀን አምስት ጊዜ የሚሰግዱ ሲሆን የዚህ መላክ ታውስ ሌላ ስሙ ሸይጣን ይባላል። ይህም በአረብኛ ሰይጣን ከሚለው ትርጉም ጋር በመገጣጠሙ በአይ ሴስ ዘንድ ያዚዲዎች ሰይጣን አምላኪ ተደርገው በስህተት እንዲፈረጁ አድርጓቸዋል።

አይ ኤስ በግልጽ ያዚዲዎችን "ሰይጣን አምላኪዎች" ብሎ የሚጠራቸው ሲሆን በዚህም ከፍተኛ ግፍ ፈጽሞባቸዋል።

አይ ኤስ ሰሜን ኢራቅን በወረረ ጊዜ 360ሺ የያዚዲ ማኅበረሰብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ መጠለያ ውስጥ ነው የቆየው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል 2ሺህ የያዚዲ ህጻናት የአይ ኤስን የግፍ ዘመን የተመለከቱ ሲሆን አሁን ጥልቅ አካላዊና ሥነልቡናዊ ምስቅልቅል ውስጥ ይገኛሉ፤ በቂ ክትትልም እየተደረገላቸው አይደለም ሲል ይወቅሳል።

ያዚዲዎች ከሰሜን ኢራቅ በተጨማሪ፣ በሶሪያና በቱርክ ይገኛሉ።