በሮማንያ የስድስት ሳምንት ልጅ ሲጠመቅ መሞቱን ተከትሎ ለውጥ እንዲደረግ ተጠየቀ

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትዓን ውስት ፀሎት የሚያደርግ ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በሮማንያ የስድስት ሳምንት ጨቅላ ሕጻን ስርዓተ ጥምቀት ከተፈፀመ ከሰዓታት በኋላ መሞቱን ተከትሎ የአገሪቱ ኦርቶዶክስ ሊቀጳጳስ እንዲህ ዓይነት ስርዓቶች ተመሳሳይ አደጋን እንዳያስከትሉ ዳግም መታየት ይኖርባቸዋል አሉ።

ጨቅላው ሕጻን በውሃ ውስጥ ሶስት ጊዜ እንዲጠልቅ ከተደረገ በኋላ የልብ ምቱ ቆሟል። ሕይወቱ ካለፈች በኋላ በተደረገለት ምርመራ ሳምባው ውስጥ ፈሳሽ የተገኘ ሲሆን፣ ስቃይ የተሞላበት ሞት መሞቱ በምርመራ ሪፖርቱ ላይ ተገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ 60 ሺህ ያህል ሰዎች ቤተክርስትያኒቱ ስርዓተ ጥምቀት የሚካሄድበት መንገድ ላይ ለውጥ እንዲደረግ ፊርማቸውን በማኖር ጠይቀዋል።

ይህ ለውጥ እንዲደረግ ከደገፉ የቤተክርስትያኒቱ አባቶች መካከል ሊቀጳጳስ ካሊኒክ ከሁሉም ከፍ ያለ የአገልግሎት ዘመን ያላቸው አባት ናቸው ተብሏል።

እኚህ አባት በአገሪቱ ለሚዘጋጅ ድረገጽ እንዳሉት ጨቅላ ሕጻናትን ውሃ ውስጥ በመጥለቅ የሚደረግ ሥርዓተ ጥምቀት ዳግም መታየት ይኖርበታል በማለት " እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ አደጋዎችን ለማስወገድ የቤተክርስቲያኒቷን ስርዓት በተከተለ መልኩ ውሳኔዎች ይሰጣሉ" ብለዋል።

የጨቅላው ህጻን ሥርዓተ ጥምቀት የተከናወነው በአገሪቱ ሰሜን ምስራቅ በምትገኘው ሱሰይቫ ከተማ ነው።

ከጨቅላው ሞት በኋላ ሥርዓተ ጥምቀቱን ያካሄደው ካህን ላይ አቃቤ ሕግ ምርመራ መጀመሩ ታውቋል።

የሮማኒያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሥርዓተ ጥምቀት የምታካሄድበትን መንገድ ለመቀየር ምልክት ማሳየቷን ተከትሎ የተለያዩ ድምጾች እየተሰሙ ነው። አንዳንዶች ይህ ቤተክርስትያኒቱ ለለውጥ ዝግጁ መሆኗን ያሳያል ሲሉ ቀሪዎቹ ደግሞ የቀደመው ሥርዓተ ጥምቀት እንዲቀጥል አብዝተው እየወተወቱ ይገኛሉ።

ሊቀ ጳጳስ ካለኒክ ከቤተክርስትያኒቱ ቀደምት አባቶች መካከል ሲሆኑ ለውጥ መካሄድ እንዳለበት በመደገፍ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ሊቀ ጳጳሱም ሥርዓተ ጥምቀቱ የሚካሄድበት መንገድ መሻሻል እንዳለበት ሲከራከሩም ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ወቅት አሁን ቤተክርስትያኒቱ በምትከተለው ሥርዓት መልክ አለመሆኑን በማስተማር ነው።

ሊቀ ጳጳስ ቶሚስ በበኩላቸው ይህ የቤተክርስትያኒቷ ሥርዓት ከሺህ ዓመት በላይ የኖረ መሆኑን በማንሳት "ለውጥ መደረግ የለበትም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ሊቀ ጳጳስ ካሊኒክ በቅርቡ ባካሄዱት ሥርዓተ ጥምቀት ወቅት ሲናገሩ እንደተደመጡት ጭንቅላትን ውሃ ውስጥ በመንከር የሚከናወን ጥምቀት ለአዋቂዎች እንጂ ለጨቅላ ህጻናት አስቸጋሪ ነው።

ከዚህ ቀደምም በዚሁ ጉዳይ ሲያስተምሩ የጨቅላ ህጻናትን እግር ብቻ በመንከር ጭንቅላታቸው ላይ በስሱ መርጨት በቂ መሆኑን ተናግረዋል።

ቤተክርስትያኒቱ ይህንን ለውጥ እንድታካሂድ የሚጠይቁ 60 ሺህ ምዕመናን እስከ አርብ እለት ድረስ ፊርማቸውን አኑረዋል።

የሮማኒያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በአገሪቱ ከፍተኛ ተቀባያነት ያላት ብትሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽንን የያዘችበት መንገድ ሲያስተቻት ነበር።